የአማራ ክልል ከአገው ሸንጎ ጋር ሲያደርገው የነበረው ውይይት አለመሳካቱ ተገለጸ

የአገው ሸንጎ በህወሃት ድጋፍ የአገው ክልልን ለመመስረት የትጥቅ ትግል እያደረገ ያለ ፓርቲ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የአማራ ክልል መንግስትም ከአገው ሸንጎ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ይልቃል ከፋለ ከሁለት ሳምንት በፊት ምክር ቤት ላይ መናገራቸው አይነጋም፡፡

ይሁንና ይህ የሰላም ውይይት አለመሳካቱን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ስቡህ ገበያው ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ላለፉት 21 ወራት በህወሓት እና በአገው ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ ታጣቂዎች ይዞታ ስር የቆየችውን የአበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማን፤ የመከላከያ ሰራዊት መልሶ ተቆጣጥሯል።

የመከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር ወደምትገኘው “ንየር አቑ” ከተማ የገባው፤ ታጣቂዎቹ አካባቢውን በትላንትናው ዕለት ለቅቀው ከወጡ በኋላ እንደሆነ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል አጎራባች የሆነው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አበርገሌ እና ጻግብጂ የተባሉት ወረዳዎቹ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነው ቆይተዋል። ጦርነቱ በተጀመረ “በአጭር ጊዜ” ውስጥ በህወሓት ታጣቂዎች እጅ ገብተው የነበሩት ሁለቱ ወረዳዎች፤  ለመጀመሪያ ጊዜ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር የገቡት የፌደራል ጦር የትግራይ ክልልን ሲቆጣጠር ነበር። 

ይሁንና የፌደራሉ መንግስት በሰኔ 2013 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ሲወጣ፤ ሁለቱ ወረዳዎች ዳግም በህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ለመውደቅ ተገድደዋል። ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር በአማራ ክልል እና አፋር ክልሎች ሲዋጋ የቆየው የመከላከያ ሰራዊት በአማጽያኑ እጅ የነበሩ በርካታ ቦታዎችን ቢያስለቅቅም፤ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር ያሉት ሁለት ወረዳዎች ግን በታጣቂዎች ተይዘው ቆይተዋል።

የአማራ ክልል መንግስት በጻግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች ያለውን ችግር ለመፍታት፤ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግር ማካሄድ መጀመሩን ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ገልጾ ነበር።

በሁለቱ አካላት መካከል በትላትናው ዕለት የተካሄደው ውይይት ትኩረት ያደረገው “በሰላም ጉዳይ” እና “ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ ስለሚቻልባቸው” መንገዶች እንደነበር የአበርገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ክፍሌ ተናግረዋል። ይህንን ውይይት ተከትሎም፤ ራሱን “የአገው ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ” በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት የዚያኑ ዕለት ንየር አቑ ከተማን ለቅቀው መውጣታቸውን አክለዋል። 

“የወረዳው ዋና ከተማ ሙሉ ለሙሉ ነጻ ሆኗል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትላንት ገብቶ አድሯል። እኛ ዛሬ እዚያው ነው ያለነው። ያለ ምንም ተኩስ፤ የመከላከያ ሰራዊት በሰላም ከተማውን ተቆጣጥሮታል” ሲሉ አቶ አለሙ በዛሬው ዕለት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል። የመከላከያ ሰራዊት ንየር አቑ ከተማ መግባቱን ተከትሎ፤ “የተወሰኑ” የታጣቂ ቡድኑ አባላት “ተሳስተን ነበር” በማለት እጃቸውን መስጠታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *