የሮበርት ሙጋቤ ልጅ ድግስ ላይ ንብረት አውድሟል ተብሎ ታሠረ

የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ወንድ ልጅ ሃራሬ ውስጥ በተዘጋጀ ድግስ ላይ ንብረት አውድሟል ተብሎ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

31 ዓመቱ እንደሆነ የሚገመተው ሮበርት ሙጋቤ ጁኒዬር ሶስት ንብረት የማውደም እና ሁለት ፖሊስ የመተናኮስ ክስ ቀርቦበታል ሲሉ ጠበቃቸው ተናግረዋል።

በድግሱ ላይ የመኪናዎች መስታወት ሲረግፍ አንድ የፖሊስ መኮንን ላይ ምራቅ መተፋቱ ተሰምቷል።

የሙጋቤ ልጅ የቀረበበትን ክስ አጣጥሎ ከደሙ ንፁሕ ነኝ ይላል።

አሁን ከእሥር ተለቆ ክሱን በድርድር ለመፍታት እየጣረም እንደሆነ ተነግሯል።

ፖሊስ በትዊተር ገፁ እንደገለጠው የሮበርት ሙጋቤ ልጅ ጓደኛ የሆነው ሲንዲሶ ንካታዞ ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ነው ፖሊስ ወደ ሥፍራው ያቀናው።

በድግሱ ላይ የደረሰው የንብረት ውድመት በገንዘብ ሲሰላ 12 ሺህ ዶላር አካባቢ ሊደርስ እንደሚችል ፖሊስ ጠቁሟል።

ሙጋቤ ጁኒዬር የቀድሞው ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ከግሬስ የወለዱት ሁለተኛ ልጃቸው ነው።

ዚምላይቭ የተሰኘው የዜና አውታር ሙጋቤ ጁኒዬር ሙሉ ልብስ ከነከረባቱ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጎ ወደ ፍርድ ቤት ሲያመራ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለቋል።

ሙጋቤ ጁኒዬር ወደ ፍርድ ቤት ሲያቀና በርካታ ሰዎች አጅቦት እንደነበር በምስሉ ላይ መመልከት ይቻላል።

ጠበቃው አሺዬል ሙጊያ አቃቤ ሕግ በቂ የሆነ ምርመራ አላደረገም ካሉ በኋላ ሙጋቤ ጁኒዬርና ቅሬታ አቅራቢ ጓደኛሞች በመሆናቸው ጉዳዩ በድርድር እንዲያልቅ ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል።

ጉዳዩ በድርድር የማይፈታ ከሆነ የቀድሞው ፕሬዝደንት ልጅ ወደ ፍርድ ቤት ተመልሶ ክሱን ይከታተላል ብለዋል ጠበቃው።

እሥርን መቃወምና የፖሊስ መኮንንን መተናኮስ የሚሉት ክሶች ውድቅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠበቃው አክለው ጠቁመዋል።

ለ37 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት የቀድሞው ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ በፈረንጆቹ 2019፣ በ95 ዓመታቸው ነው ከሥልጣን በኃይል የወረዱት።

ዚምባብዌ በ1970ዎቹ ሮዴሺያ ተብላ ስትጠራ ሳለ የነበረውን የነጮች አገዛዝ በመታገል የሚታወቁት ሙጋቤ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጉልበት በመጠቀም ምርጫ አሸንፈዋል፤ የዚምባብዌን ምጣኔ ሃብት አድቀዋል ተብለው ይወቀሳሉ።

የሃገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞች ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን ላይ ቢሆኑ ኖሮ ልጃቸው ለእሥር አይዳረግም ነበር ሲሉ ይተነትናሉ።

ሙጋቤ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ በቀድሞው አጋራቸው ኤመርሰን ምናንጋግዋ ተተክተዋል።

በምናንጋግዋና በሙጋቤ ቤተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረው ኤመርሰን፤ ሙጋቤን ክዷቸዋል የሚሉ ወሬዎች መሰማት ከጀመሩ በኋላ ነው።

የሙጋቤ የቀድሞ ሚስት ግሬስ ባላቸውን ለመተካት ሐሳብ የነበራቸው ሲሆን በምናንጋግዋ ደጋፊዎች ድጋፍ ተነፍገዋል።

ነገር ግን ሙጋቤ ጁኒዬር ከፕሬዝደንት ምናንጋግዋ ጋር ያለውን ግንኙነት በማለሳለስ ባለፈው ዓመት ገዢውን ፓርቲ [ዛኑ-ፒኤፍ] ተቀላቅሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *