አቡነ ማትያስ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትግራይ ተጓዙ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ከቆመ ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀለ ገቡ።

ፓትሪያርኩ ወደ ትግራይ ያቀኑት ከቀናት በፊት በሞት በተለዩት የመቀለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጻጻስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የሽኝት ሥነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው።

አቡነ ማቲያስ ለሁለት ዓመት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወደ ትግራይ ሲያመሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ፓትሪያርኩ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ በይፋ ሲናገሩ የነበረ ሲሆን ሰላም እንዲወርድም በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።

ነገር ግን በትግራይ ክልል ያሉ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች በጦርነቱ ጊዜ በትግራይ ውስጥ ባሉ ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰውን ጉዳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አላወገዘችም ከጎናችንም አልቆመችም በማለት እራሳቸውን ማግለላቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በዚህም የትግራይ ቤተክህነት መመስረታቸውን በመግለጽ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክረስቲያን መለየታቸውን አሳውቀው ነበር።

ደም አፋሳሹ ጦርነትን ያስቆመው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከተፈረመ ከወራት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በትግራይ ካሉ አባቶች ጋር ግንኙቷን ለማሻሻል ፍለጎት እንዳለት በደብዳቤ ገልጻ ነበር።

ነገር ግን በትግራይ ያሉት የሃይማኖቱ መሪዎች ቀደም ሲል ያቀረቧቸውን ምክንያቶች እና ሌሎችንም በመጥቀስ በመለየት ውሳኔያቸው እንደሚቀጥሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የካቲት 21/2015 ዓ.ም. ማረፋቸው በተገለጸው በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ወደ መቀለ ዛሬ መቀለ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ሲደርሱ በክልሉ ባሉ የሃይማኖት አባቶች ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተዘግቧል።

አቡነ ማትያስ በትግራይ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከመሳተፍ ባሻገር ሌላ የተያዘላቸው መረሃ ግብር ስለመኖሩ ከጽህፈት ቤታቸው የተባለ ነገር ባይኖርም፣ በክልሉ ካሉ የቤተክርስቲኣኗ አባቶች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *