ኢትዮጵያ የ 1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ዕዳዋን ለማዋቀር ስታደርግ የነበረዉ ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በ2024 ዓ.ም. ዋናው ዕዳ የሚከፈልበት የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቦንድ ዕዳዋን ለማዋቀር ያደረገው ወሳኝ ጥረት ከቦንድ ባለቤቶች ተወካዮች ጋር ሲያደርገው የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ለዚህ ብድር በየዓመቱ 6.625% ወለድ ለመክፈል መስማማቷ ይታወቃል።
የገንዘብ ሚኒስትር እንዳስታወቀው በመስከረም 15 እና ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም መካከል የተካሄደው ውይይት በሁለቱ ወገኖች የቀረቡትን የመጨረሻ የዕዳ ማዋቀር ሃሳቦች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ አልተቻለም።
ሚኒስቴሩ ድርድሩ በዚህ ጊዜ ሳይሳካ ቢቀርም፣ “ሰፊ መሻሻል” መመዝገቡን ገልጾ፣ ውይይቱ ወደፊት እንደሚቀጥል ተስፋውን አጠናክሯል።
ሁለቱም ወገኖች ለአዲሱ ቦንድ እትም ዋናውን ዕዳ በ15% ቅናሽ በማድረግ 850 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን፣ የክፍያ የመጨረሻ ቀኑ ሐምሌ 15 2029 እንዲሆን እና ያለፉት ሶስት የወለድ ክፍያዎች በሙሉ 99.375 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈሉ በሚለው ላይ ተቀራርበው ነበር።
ሆኖም፣ ቁልፍ ልዩነቶች በተለይም በቀረበው የእሴት መልሶ ማግኛ መሣሪያ እና “የኪሳራ ቅነሳ” ውሎች ዙሪያ ቀርተዋል።
ሁለቱም በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ የተመሠረተ የእሴት መልሶ ማግኛ መሣሪያ ቢጠቁሙም ፣ ባለቤቶቹ ከተጨማሪ የወጪ ንግድ በ4 ዓመታት ውስጥ 4.75% ከፍተኛ ክፍያ ሲፈልጉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ለረጅም ጊዜ (እስከ 2035/36) የሚቆይ እና በ1.5% የተገደበ ዝቅተኛ ክፍያ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ ዕዳዋን እንደገና ለማዋቀር ከግል ባለቤቶች ጋር ሚስጥራዊ ውይይት የጀመረችው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት የ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮቦንድ ዕዳን እንደገና ለማዋቀር (restructure) ከዓለም አቀፍ የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ጋር ይፋዊ እና ሚስጥራዊነትን ያካተተ ውይይት እንደተጀመረም በወቅቱ ተገልጾም ነበር።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ እዳ እንዳለባት የዓለም ባንክ ሪፖርት ያስረዳል።
ቻይና፣ የዓለም ባንክ፣ አድሪካ ልማት ባንክ፣ አይኤምኤፍ እና ሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ለኢትዮጵያ ብድር ያቀረቡ ሀገራት እና ተቋማት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።