የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሼን ባለፉት 2 ዓመታት ኢትዮጵያ ከውጪ የምታገኘው እርዳታ ማሽቆልቆሉን ባደረግሁት ጥናት አረጋግጫለው ብሏል።
በተለይ ከ4 ዋና ዋና አበዳሪዎች ማለትም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ለተከታታይ 3 ዓመታት የተገኘው እርዳታ እንደቀነሰ በጥናቴ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በየጊዜው ለኢትዮዽያ ኢኮኖሚ የሚበጀውን ሀሳብ የሚያዋጣውና የሚመክረው የኢትዮዽያ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪዎች እና አጥኝዎች ሰሞኑን በኢትዮዽያ የውጪ እዳ ጫና እና እርዳታ መዳከም ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በተለይ ለኢትዮዽያ ይደረግ የነበረው የውጪ እርዳታ መቀነሱ የሚያመጣው ጫና እንዳለ በጥናቱ መብራራቱ ታውቋል።
በህፃናት፣ በፋይናንስ አካታችነት፣ በወጣቶች ስራ ፈጠራ፣ በሴቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች የተቋረጠው እርዳታ ምን ጫና አመጣ ኢትዮዽያስ ምን ማድረግ ይኖርባታል በሚለው ጉዳይ ምሁራኑ መክረዋል።
አዲስ ካሳሁን (ዶ/ር) በኢትዮዽያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የአለም አቀፍ እርዳታ በዚህ ሁለት ዓመት በጣም እየወረደ መሆኑን ጠቅሰው በሁለት ዓመት ውስጥ ከ 9 እስከ 17 በመቶ ማሽቆልቆሉን ነግረውናል።
ይህም በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር ጥናቱ አሳይቷል ተብሏል።
በኢትዮዽያ ጥብቅ የገንዘብ ስርዓት ፖሊሲ በመተግበሩ የዋጋ ግሽበቱ እንደቀነሰ፣ ተጠባባቂ የውጪ ምንዛሪ ክምችት መጨመሩ እና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚው ለውጥ እንደመጣበት በመንግስት በኩል ተደጋግሞ መነገሩ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሀገራት መካከል ከዩክሬን በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር ነች።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ዩኤስኤይድ ከአስቸኳይ የሰብዓዊ መብት ድጋፎች ውጪ ቀሪ ፕሮግራሞቹን አቋርጧል።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን መበተን፣ ይሰሯቸው የነበሩ ፕሮግራሞችን ማቋረጥ እና እስከመዘጋት መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል።
የኢትዮጵያ መንግስትም የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን ለመደገፍ ኢትዮ ኤይድ የተሰኘ ድርጅት አቋቁሟል።
ይህ በዚህ እንዳለም የስደተኞችና ተመላሾች ዳይሬክተር ጀኔራል ጠይባ ሐሰን፣ ለጋሾች ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞች የሚሠጡት ድጋፍ መቀነሱ አሳሳቢ መኾኑን ጀኔቫ ውስጥ ሰሞኑን በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ሀላፊዋ አክለውም በቂ ዓለማቀፍ ድጋፍ ሳይኖር ኢትዮጵያ በየጊዜው ቁጥራቸው የሚጨምር ደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞችን በመቀበል ላይ ናትም ብለዋል።
የተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ለኢትዮጵያ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበርም ጠይባ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳናዊያን በተጨማሪም ኤርትራውያን ፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣ የመን እና ሌሎችንን ሀገራት በድምሩ አንድ ሚሊዮን ስደተኞችን አስጠልላለች።