የዓለም ባንክ ባወጣው አዲስ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ በቅርቡ የገባው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በሚደረገው ውድድር ፍትሃዊ ያልሆነ የመጫወቻ ሜዳ እንደገጠመውና ለከፍተኛ ኪሳራ እንደተዳረገ ይፋ አድርጓል።
“የኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ግምገማ” በሚል ርዕስ የቀረበው ይህ ሪፖርት፣ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ ውድድር በዝርዝር ይተነትናል።
ሪፖርቱ እንደሚለው፣ ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ሳፋሪኮም 850 ሚሊዮን ዶላር የፈቃድ ክፍያ ባለመክፈሉና በስድስት የገበያ ዘርፎች ላይ የበላይነት ያለው ተቋም (SMP) ሆኖ በመቆጠሩ ውድድሩ ፍትሃዊ አይደለም።
ኢትዮ ቴሌኮም ከደንብ አስከባሪው ከተቀመጠው የመገናኛ ዋጋ (MTR) በታች የድምጽ ጥሪ ዋጋ በማቅረቡ፣ ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች በሚደረግ እያንዳንዱ ጥሪ ላይ ኪሳራ እንደሚያስተናግድ ሪፖርቱ ገልጿል (በወር 1.6 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል)።
በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም የዳታ ዋጋን በእጅጉ በመቀነስ ውድድሩን ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል።
ሪፖርቱ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ እንደ M-Pesa ያሉ የሳፋሪኮም መተግበሪያዎችን እንዳገደና በመንግስት የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ላይ የመንግስት ድርጅቶች ምርጫ ሊሰጠው እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
ሳፋሪኮም በኢትዮ ቴሌኮምና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመሰረተ-ልማት አውታሮች ላይ ጥገኛ መሆኑና ለኪራይ በዓመት 3 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮ ቴሌኮም መክፈሉ የኔትዎርክ መስፋፋቱን አዝጋሚና ወጪውን ከፍተኛ እንዳደረገበት ተጠቅሷል።
በእነዚህ ተግዳሮቶች ምክንያት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ2024 በጀት ዓመት 325 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ያገኘው 53.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ ለፈቃድ በዓመት የሚከፍለውን 66.7 ሚሊዮን ዶላር እንኳን እንደማይሸፍን ሪፖርቱ አብራርቷል።
ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እነዚህን ፍትሃዊ ያልሆኑ የውድድር ሁኔታዎች እንዲያጣራና እንዲያስተካክል ጠይቋል።
በተጨማሪም፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ለማስፋት እንደ ስታርሊንክ ላሉ የሳተላይት ኦፕሬተሮች ፈቃድ እንዲሰጥ ሀሳብም አቅርቧል።
የዓለም ባንክ ሪፖርት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ተግዳሮቶች ይፋ ያደረገ ሲሆን ኩባንያው በ2024 325 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አስመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ለውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በሯን መክፈቷን ተከትሎ ነበር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡
ድርጅቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ለኢትዮጵያ በሚል ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ህጋዊ ፍቃድ ከተቀበለ ከአንድ ዓመት በኋላ ስራ ጀምሯል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለኔትወርክ ማስፋፊያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድቤያለሁ ብሏል፡፡