ኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ ዕዳዋን እንደገና ለማዋቀር ከግል ባለቤቶች ጋር ሚስጥራዊ ውይይት ጀምራለች።
የኢትዮጵያ መንግስት የ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮቦንድ ዕዳን እንደገና ለማዋቀር (restructure) ከዓለም አቀፍ የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ጋር ይፋዊ እና ሚስጥራዊነትን ያካተተ ውይይት መጀመሩን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ይህ እርምጃ ሀገሪቱ በከባድ የዕዳ ጫናዋን ለማቃለል በምታደርገው ጥረት ውስጥ እንደ ወሳኝ ምዕራፍ ተወስዷል።
ውይይቱ “restricted” ተብሎ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ማለት በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት አበዳሪዎች (የቦንዱ ባለቤቶች) “የምስጢራዊነት ስምምነት” (NDA) መፈረም ነበረባቸው።
ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግስት ለስምምነቱ መሳካት ወሳኝ የሆኑ ሚስጥራዊ የኢኮኖሚ መረጃዎችን ለአበዳሪዎቹ እንዲያካፍል ያስችለዋል።
ስምምነቱን የፈረሙ ባለቤቶች በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያን ቦንድ መሸጥም ሆነ መግዛት አይችሉም።
ይህ የውይይት እርምጃ የመጣው ኢትዮጵያ በ2023 መጨረሻ ላይ የነበረውን የዩሮቦንድ ክፍያ ማዘግየቷን ተከትሎ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በG20 የጋራ ማዕቀፍ ስር የዕዳ ማቃለያ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ይህ በዚህ እንዳለም መንግሥት የ243 ቢሊዮን ብር ቦንድ ጨረታ አውጥቷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ለሶስት ወራት የሚቆይ የ243 ቢሊዮን ብር የግምጃ ቤት ሰነዶች ጨረታ አውጥቷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2025 የመጨረሻ ሩብ ዓመት የሚካሄደውን ጠንካራ የግምጃ ቤት ሰነዶች (T-Bills) የጨረታ መርሃ ግብር ይፋ ማድረጉን አስታውቋል።
ከመስከረም 21 እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚካሄደው ይህ የሶስት ወራት መርሃ ግብር በአጠቃላይ 243.05 ቢሊዮን ብር የሚገመት የዕዳ ሰነድ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ቀርቧል።
መንግሥት የሀገር ውስጥ የዕዳ ገበያን ለማሳደግ በያዘው የፋይናንስ ማሻሻያ አጀንዳ ውስጥ ቁልፍ እርምጃ መሆኑ ተመላክቷል።
በተለይም ይህ የዕዳ ሰነድ አቅርቦት በየሁለት ሳምንቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ ለባንኮች፣ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ለጡረታ ፈንድ እና ለሌሎች ተቋማት የተረጋጋ የኢንቨስትመንት ዕድልን ይፈጥራል ተብሏል።
ባለሀብቶች በአራት የተለያዩ የጊዜ ገደቦች ማለትም 28 ቀናት፣ 91 ቀናት፣ 182 ቀናትና 364 ቀናት ላይ መጫረት እንደሚችሉም ተገልጿል።