በተሻሻለው የትራምፕ ታሪፍ ኢትዮጵያ ቀድሞ በተጣለባት ዝቅተኛው 10 ፐርሰንት ታሪፍ እንድትቀጥል ተደርጓል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሥርተ ዓመታት የቆዩትን የዓለም ንግድ አሠራሮች ለመለወጥ በሚያደርጉት ጥረት ከሰባ በላይ አገራት ላይ አዲስና የተቀየረ የንግድ ቀረጥ ተግባራዊ ሊያደርጉ መሆኑን አስታወቀዋል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ የተጣለባትን የ10 በመቶ ታሪፍ የተቀበለች ሲሆን ታሪፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንደሚያሳድግላት አስታውቃለች።
ትናንት በተፈረመው የአስፈጻሚ ትዕዛዝ መሰረት፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአገሪቱን የንግድ ጉድለት ከዋነኛ አጋሮች ጋር ለመቀነስ ታስቦ የተደረገ ነው በማለት የገለፁ ሲሆን፣ በዚህም እስከ 41 በመቶ የሚደርስ አዲስ የገቢ ምርቶች ላይ የሚጣል ታሪፍን ተፈፃሚ አድርገዋል።
በካናዳ ምርቶች ላይ የተጣለው የንግድ ቀረጥ ወደ 35 በመቶ ከፍ ማለቱ ቀድሞውንም የተወጠረው የንግድ ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻክር ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።
ታይላንድ እና ካምቦዲያ በበኩላቸው የመጨረሻ ሰዓት ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ 19 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባቸዋል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ሜክሲኮ የተሻሻሉ የንግድ ውሎችን ለመደራደር የ90 ቀናት ጊዜ ተሰጥቷታል።
ዋይት ሃውስ እንዳረጋገጠው በሚያዝያ 9 የተወሰነው “ሁለንተናዊ” ቀረጥ በ10 በመቶ እንደሚቆይ ነው። ነገር ግን፣ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ትርፍ ያላቸው አገራት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቶችን ለመለወጥ በሚያደርጉት ሰፊ ጥረት 15 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የጨመረ ቀረጥ ይጣልባቸዋል።
በኒው ዚላንድ ምርቶች ላይ የተጣለውን የ15 በመቶ ቀረጥ በተመለከተ፣ አገሪቱ ውሳኔው እንዲከልስላት ለመጠየቅ ማቀዷን አስታውቃለች።
ዋይት ሃውስ እንዳስታወቀው፣ አዲሱ የንግድ ቀረጥ ከስድስት ቀን በኋላ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ ለዓለም ኢኮኖሚ አዲስ ፈተና ከመፍጠሩም ባሻገር የአሜሪካን አጋርነቶች ጥንካሬ ይፈትናል ተብሏል።