የቻይና ጉምሩክ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ቻይና ከአሜሪካ ጋር እየተካረረ የመጣውን የንግድ ውጥረት ተከትሎ የፕሮቲን አቅርቦቶቿን ለማስፋት ባላት ፍላጎት ከኢትዮጵያ የሚገቡ የአኩሪ አተር ምርቶችን እንዲገቡ ፈቃድ መስጠቷን ኒውስ ሴንትራል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አኩሪ አተር ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ቻይና እንዲገቡ ተፈቅደዋል።
ቻይና ለአገር ውስጥ የአኩሪ አተር ምርት በአብዛኛው በአኩሪ አተር ምርቶች ከብራዚል እና ከአሜሪካ ታስመጣለች።
ቻይና በሰኔ ወር ከኡራጓይ የሚገቡ የአኩሪ አተር ምርቶች እንዲገቡ ፈቅዳለች፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አሁን ሩሲያ፣ ቤላሩስ፣ አርጀንቲና እና ብራዚልን ጨምሮ እውቅና የተሰጣቸውን የአቅራቢዎች ዝርዝርን ተቀላቅላለች።
ቻይና የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋር ስትሆን ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ መጠን ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።
ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ወደ ቻይና የምትልከው ቡና በየ ዓመቱ የ27 በመቶ እድገት አሳይቷል።
ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ከቡና በተጨማሪም ሰሊጥ፣ ማዕድናት እና ሌሎች ምርቶችን ስትልክ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን፣ የፋብሪካ ግብዓት፣ ኬሚካል እና ሌሎች ምርቶችን ደግሞ ከቻይና ትገዛለች።
ከአምስት ሺህ በላይ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስክ ተሰማርተው እየሰሩ ሲሆን በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ብቻ ከአራት ቢሊዮን ዶላር ሀብት ያላቸው ድርጅቶች በስራ ላይ እንደሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መረጃ ያስረዳል።
ከቻይና በመቀጠል ሕንድ፣ ቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ኩባንያዎች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከወጪ ንግድ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን ከቡና ንግድ ብቻ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ከወርቅ ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ቀዳሚ ናቸው።