በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች በወሲብ ንግድ መሰማራታቸው ተገለጸ

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ኑሮን ለማሸነፍ ስላላስቻላቸው ማታ ማታ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ መኖራቸውን በጥናት መለየቱን የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ ለኑሮ ስለማይበቃቸው ማታ ማታ ከሆቴሎች ትርፍራፊ ምግቦችን ይዘው ወደ ቤታቸው የሚገቡ እንዳሉም ፌደሬሽኑ ጠቁሟል፡፡

አምራች ስራተኛ፣ ምቹ ስራ ለወጣቶች እና ሴቶች በጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ መፍጠር በሚል ርዕስ የፖሊሲ አቅጣጫ ጠቋሚ ጥናት ለማድረግ የማህበራት ጥናት መድረክ (Forum For Social Studies) በጠራው የሁለተኛ ዙር የባለድርሻ አካላት ወይይት ላይ የተገኙት የጨርቃ ጨርቅ ፌዴሬሽን ተወካይ አቶ ተስፋዬ አብዲሳ ‘’የሚከፈላቸው ደመወዝ ለኑሮ ስለማይበቃቸው ማታ ማታ ከሆቴሎች ተመላሽ ምግቦችን ይዘው የሚገቡ እንዳሉም በጥናት አረጋግጠናል’’ ማለታቸውን ሸገር ሬዲዮ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ስራተኞች ገቢ እንዲሻሻል ለማድረግ  ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ማፅደቅ አንዱ መፍትሄ ነው፤ ያሉት ተወካዩ ‘’በተለይ ሴቶች ክፍያው ዝቅተኛ ስለሆነ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ መኖራቸውን በጥናት አረጋግጠናል’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ባካሄደው ጥናት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ አሰሪዎች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ፈቃደኞች እንዲሆኑ አረጋግጧል ተብሏል፡፡

መንግስት ግን በጉዳዩ ዙሪያ እልባት ለመስጠት የሚዘገይበት ምክንያት ግልፅ አይደለም ተብሏል፡፡

ሌላ የውይይት ተሳታፊ በበኩላቸው በኢንዲስትሪ ፓርኮች በጨርቃ ጨርቅ እና ጋርመንት ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሴት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ በትዳር ሕይወታቸው ላይ እንኳን የመወሰን መብት እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለዋል፡፡

ትዳር የሚመሰርቱት ስለፈለጉ ሳይሆን ወጪ ለመጋራት በሚል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አማካሪ አቶ ዘሪሁን ገዛኸኝ በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን መጠየቅ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ሆኖታል እስካሁን ግን መፍትሄ አላገኘም ብለዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ወርሃዊ ክፍያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲተያይ እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት ደግነት አበባው (ዶ/ር) በበኩላቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ አስፈላጊነቱ እንዳማያጠራጥር ተናግረው ነገር ግን እንዴት ይወሰን የሚለውን በደንብ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ነገ ሀሙስ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ136ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰራተኞች ቀንን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ የዝቀተኛ ደመወዝ ወለል እንዲወስን የጠየቀው ጥያቄ መልስ እንዳላገኘለት ተናግሯል፡፡

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ተጠይቆ የዝቀተኛ ደመወዝ ወለል ጉዳይ ከሀገሪቱ ዋና ኢኮኖሚ ጋር የሚገናኝ ስለሆነ በጥንቃቄ ነው መታየት ያለበት የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *