የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ባንኮች የምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድደውን ህግ ተቃወመ

ባንኮች እስከ ምሽት 3፡30 ሰዓት ድረስ ክፍት እንዲሆኑ የሚያስገድደዉ ደንብ ከባንኮች አሰራር ጋር የማይጣጣም ነዉ ሲል የባንኮች ማህበር አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣው ባንኮች እስከ ምሽት 3:30 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድደው መመሪያ ከባንኮች አሠራር ጋር የማይጣጣም መሆኑን ማህበሩ ገልጿል፡፡

ባንኮች በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አማካይነት የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞቻቸው በቀላሉ ማቅረብ እየቻሉ በመሆኑ፣ የምሽት አገልግሎት አላስፈላጊና አግባብነት የሌለው መሆኑን የባንኮች ማህበር አስታዉቋል።

የባንኮች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ደምሰው ሞገስ እንደሚገልጹት፣ደንበኞች በፖስ ወይም ኤቴኤም ማሽኖች፣ በተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ መተግበሪያዎችና በኢንተርኔት ባንኪንግ አማካይነት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ስለሚችሉ ባንኮች እስከ ምሽት ክፍት ሆነው መቆየት አለባቸዉ የሚለዉ አስገዳጅ መመሪያ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ማህበሩ በፌዴራል መንግሥት ሥር ያሉ ተቋማትን የከተማ አስተዳደር በመመሪያ እንዲያስተዳድር የተሰጠው ሥልጣን አግባብ እንዳልሆነና ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተያየት መጠየቅ እንደነበረበት ይገልጻሉ።

በተለይም ይህ መመሪያ የባንኮችን የስራ ባህሪ  ያላገናዘበና ለባንኮችም ሆነ ለደንበኞች ደህንነት አስጊ ሊሆን የሚችል መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሃፊው በምሽት የሚሰጥ የባንክ አገልግሎት ለዘረፋና ለሌሎች የደህንነት ስጋቶች ሊያጋልጥ እንደሚችል ተናግረዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ደምብ 185/2017 የተሰኘ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምሽት 4 ሰዓት ድረስ በመንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ እስከ ምሽት 3:30 ሰዓት ድረስ እንዲቆዩ የሚያስገድድ ደምብ ከየካቲት 29 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከቀን የስራ ሰዓት ባለፈ ምሽት እና ሌሊት ላይ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መንግስት ጨና በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የከተማዋ አስተዳድር የመንግስት ተቋማት በሌሊት ፈረቃ አገልግሎት እንዲሰጡ እንቅስቃሴ ከጀመረ አንድ ዓመት ያለፈው ቢሆንም ተቋማቱ እስካሁን አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም፡፡

እንዲሁም የተወሰኑ መንግስታዊ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለሶተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት አገልግሎቶችን የማዘመን እና ቀላል ለማድረግ እቅድ እንዳውም ከዚህ በፊት ተገልጿል፡፡

ይህም አገልግሎት ፈላጊ ዜጎች እንዳይንገላቱ፣ ለሙስና እና ሌሎች ጉዳቶች እንዳይጋለጡ ያደርጋል ቢባልም አገልግሎቶቹ እስካሁን አልተጀመሩም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *