የታክስ ዕዳ ያለባቸው 62 ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ ታገዱ

ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ዕዳ ያለባቸው 62 ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ፡፡

የግብር ዕዳ ያለባቸውና በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ዕዳቸውን ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ 62 ግለሰቦችን ላይ ነው ትዕዛዙ የተላለፈው::

በዚህም ቢሮው በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ ከ1-3 ለተቋሙ በተሰጠ ስልጣን መሰረት ከሀገር እንዳይወጡ ለፌዴራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዝርዝራቸውን ማስተላለፉን አሳውቋል፡፡

ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የግብር ዕዳቸውን በአግባቡ ሳይወጡ የሚሰወሩ ግብር ከፋዮችን በመከታተል ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የዕዳ ክትትልና አስተዳደር የስራ ክፍልን በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቋል::

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡

ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ቢሮው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ የግብር ገቢ የሚሰበሰብባት ከተማ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ምክረ ሀሳብ መሰረት ገቢ የሚሰበሰብባቸውን መንገዶ እያሰፋች ትገኛለች፡፡

መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን በጀት የመደበ ሲሆን ከታክስ የሚሰበስበውን ገንዘብ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *