የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ ለስፑትኒክ አፍሪካ እንደተናገሩት፤ ተሽከርካሪዎቹ ከሀገሪቱ መልክዓ ምድር ጋር አብረው የሚሄዱ እና የዩሮ 5 የሞተር የተገጠመላቸው በመሆኑ የአየር ብክለት ተፅእኗቸው አነስተኛ ነው።
በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ዩሮ 2 እና ዩሮ 3 የሞተር ብቃት ያላቸው ሲሆኑ፤ ሩሲያ ሰራሾቹ ካማዝ ተሽከርካሪዎች ግን በዚህ ረገድ አዲስ ምዕራፍን የገለጡ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ የንግድ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እንዳገዛቸውም ነው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንቱ የተናገሩት።
ተሽከርካሪዎቹን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባው የባዝራ ሞተር ድርጅት ማናጀር ያይራድ አስናቀ በበኩላቸው፤ ተሽከርካሪዎቹ በ2025 የመጀመሪያ አጋማሽ ወር ወደ ኢትዮጵያ መግባት ይጀምራሉ ብለዋል። በቀጣይ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችንም ጭምር ለማስገባት እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነም ለስፑትኒክ አፍሪካ ጨምረው ገልጸዋል።
የሩሲያ የመኪና አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆኑ በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ከሩሲያ የላዳ እና ጋዝ ግሩፕ መኪና አምራች ኩባንያዎች የመጡ ተወካዮች ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ለተወካዮቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ፣ ስለዘርፉ ማበረታቻዎች እንዲሁም በአፍሪካ ግንባር ቀደም ስለሆነው የድሬዳዋ የነጻ ንግድ ቀጠና አጠቃላይ ገለጻ እንደተደረገላቸውም ተገልጾም ነበር፡፡
የመኪና አምራች ኩባንያ ኃላፊዎቹ ከድሬዳዋ በተጨማሪ የቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የስራ እንቅስቃሴና የምርት ሂደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካና የአፍሪካ ገበያዎች ለጤና ተቋማት፣ ለፀጥታ አካላት፣ ለጭነት አገልግሎት እንዲሁም ለግልና ለህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚውሉ የተለያየ ሞዴል ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ ታዋቂ መሆናቸው ይታወቃል።
ተወካዮቹ በተለይም በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት በማድረግ የተለያዩ ምዴል ምርቶችን በኢትዮጵያ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል ።
ሩሲያ በኢትዮጵያ የመኪና ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀድመው የሚታወቁ ሲሆን በተለይም ላዳ የተሰኘችው መኪና ሞዴል በኢትዮጵያ ከተሞች የተለመዱ ናቸው፡፡