በክቡር ገና
በሀገራችን “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል” የሚል ምሳሊያዊ አነጋገር አለ፡፡ አጋም እሾሀማ ተክል ሲሆን ቁልቋል ደግሞ ለመወጋት የተመቸ ጠፍጣፋ ቅጠል መሰል አካል ያለው ተክል ነው፡፡ አጋሙ በጠንካራ እሾሁ ቁልቋሉን ሲወጋው ልክ ህመሙ ያሰቃየው ይመስል ከጠፍጣፋ አካሉ እንደ እንባ ነጭ ፈሳሽ ያነባል፡፡ እናም “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል” የተባለውም ለዚህ ነው፡፡
ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ እንደሚኖር ሁሉ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የተጠጋም ሀገር ያለጥርጥር ሲያለቅስ ይኖራል፡፡ ከአይ ኤም ኤፍ ተጠግተው ሲያለቅሱ የኖሩ በርካታ ሀገራትን መጥቀስ ቢቻልም አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ናይጄሪያና ዛምቢያ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ተራው የኢትዮጵያ ነው፡፡
በቅርቡም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዎሪጄቫ ኢትዮጵያን ጎብኝተው “ በአዲስ አበባ ከተማ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የማየው በፈገግታ የተሞላ ፊት ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ ምጸት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያም ፌዝ ነው፡፡ የተቋሙም ኢኮኖሚያዊ ትንታኔም ልክ የዳይሬክተሯን አስተያየት የመሰለ ነው፡፡
ተቋሙ ለሁሉም በሽታዎች አንድ አይነት መድሀኒት ከሚያዝ ሀኪም ጋር ይመሳሰላል፡፡ ለሁሉም የሚያዛቸው መድሀኒቶች ደግሞ
ወጪ መቀነስ
የውጭ ምንዛሪ ተመነን በገባያ ዋጋ መሰረት ማድረግ
ገበያ ሁሉንም ነገር እንዲወስን ማድረግ ናቸው፡፡
የተከበረው አቶ አይ ኤም ኤፍ ያንን ሁሉ ኤክስፐርቶችና ሊቃውንትን አሰባስቦም እንኳ የሚያሻሽለው ወይም የሚቀይረው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ችግሩን ሲያባብሰው ነው የሚታየው፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተቋሙ የግብር ይውጣ እርምጃ መፍትሄ የሚያገኝ ቀላል እራስ ምታት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገደል አፋፍ ላይ የቆመ ሲሆን አይ ኤም ኤፍ ደግሞ ለሀገሪቱ መፍትሄ ብሎ እያቀበለ ያለው የተቀዳደደ ፓራሹት ነው፡፡
ሀምሌ 21/ 2016 ዓ.ም ይፋ በተደረገው በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት እንጀምር፡፡ ይህ ብርን የማንሳፈፍ እርምጃ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከነበረበት ቦታ ወድቆ እንዲፈጠፈጥ ነው ያደረገው፡፡ በዚህ እርምጃ የብር የመግዛት አቅም በ100 ፐርሰንት አንዲዳከም ሆኗል፡፡ ይህም እንደ ድል ተቆጥሮ መደበኛው የዶላር ምንዛሪ ከትይዩ ገበያው እኩል ሆነ ተብሎ ከበሮ ተደለቀ፡፡ ገበያው ተረጋጋም ተባለ፡፡ ሆኖም ግን ገበያው ተረጋግቶ ሳይሆን ውሀ ሲወስድ አሳስቆ አንደሚባለው ሆኖ ነው፡፡
ተቋሙ እርምጃውን ቢያወድስም እንደ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ማህበር ያሉ ተቋማት ግን የአይ ኤም ኤፍን ሀሳብ አልገዙትም፡፡ ማህበሩ በሩብ አመቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንተናው ሀገሪቱ የገጠማት ችግር ሁል አቀፍ የኢኮኖሚ መንኮታኮት ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን ጠቅሶ ይህም ችግር እንደ ጊዚያዊ ችግር እንጂ ስር የሰደደ መዋቅራዊ ችግር ተደርጎ መታየት እንደሌለበት አመልክቷል፡፡
የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ግምግማ ግን ከዚህ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ዘርፈ ብዙና ሁለንተናዊ መሆኑን ጠቅሶ በገበያ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአትን ጨምሮ፣ የወጪ በጀትን መቀነስንና ሌሎች ማሻሻያዎችን የሚያካትት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አስፈላጊ ነው ሲል ይተነትናል፡፡
በውጤቱም የዋጋ ንረቱ ሰማይ ነካ፣ የገቢ ንግድ ዋጋ እጥፍ ሆነ፣ አይ ኤም ኤፍን ድረስልን ብሎ ያልጋበዘው የኢትዮጵያ ህዝብ በመጠነኛ ገንዘብ ይሸምተው የነበረው የሸቀጥ ዋጋ የትየለሌ ሆነ፡፡ ይብሱኑ ደግሞ በሁለተኛው የተቋሙ ግምገማና በተቋሙ ዋና ዳይሬክትር ጉብኝት ወቅት ያው የተለመደው “ ቀበቷችሁን አጥብቁ” የሚለው ምክረ ሀሳብ በቀጭን ትእዛዝ መልክ ጎልቶ ተሰምቷል፡፡
በተቋሙ ሁለተኛው ግምገማ ኢትዮጵያ ከተቋሙ ተከታታይ የገንዘብ ድጋፍ ታገኝ ዘንድ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦች ተቀምጠዋል፡፡ ምክረ ሀሳቦቹም ጥብቅ የበጀት ፖሊሲን ተግባራዊ ማድግ፣ ገበያውን ለውድድር ክፍት ማድረግ፣ የውጭ እዳን በወቅቱና በአግባቡ መክፈል የመሳሰሉ ሲሆኑ ምክረ ሀሳቦቹ ከሀገሪቱ የልማት ፍላጎት ይልቅ ለአለም አቀፍ አበዳሪዎች ትኩረት የሰጠ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ለተቋሙ ኢትዮጵያ ከጦርነት በኋላ መልሶ ለመቋቋም የምታደርገው መፍጨርጨር፣ የድርቅ አደጋን ለመቋቋም የምታደርገው ጥረትና በፖለቲካ አለመረጋጋት እየደረሰባት ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መናወጥ ከቁብ የሚቆጠር አይደለም፡፡ እናም ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራልና እነሆ ኢትዮጵያም ከአይ ኤም ኤፍ ተጠግታለችና ስታለቅስ ትከርማለች፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው ተቋሙ ለሁሉም በሽታዎች አንድ አይነት መድሀኒት ከሚያዝ ሀኪም ጋር ይመሳሰላል ባልነው መሰረት “ ቀበቷችሁን አጥብቁ” የሚለው ምክረ ሀሳብ ለሁሉም ከተቋሙ ለተጠጉ ሀገሮች የሚቀርብ ቀጭን ትእዛዝ ሲሆን ቀበቶ ማጥበቁ ለማን ጥቅም የሚለው ግን ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ ቀበቷችንን የምናጠብቀው እራሳችንን ችለን ቀና ብለን ለመራመድ ሳይሆን የአይ ኤም ኤፍ አደግዳጊ ሎሌ ለመሆን ነው፡፡ ተቋሙ ኢትዮጵያ ቀበቶዋን እንድታጠብቅ የሚያዘው ሀገሪቱ ከውጭ የተበደረችውን ገንዘብ ሳታስተጓጉል በወቅቱ እንድትከፍል አንጂ ሀገሪቱ መድሀኒት፣ ምግብና ነዳጅ ለመግዛት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ አይደለም፡፡
እዚህ ላይ የተቋሙን ስጋትም መዘንጋት የለብንም፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 29 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ብድር ያለባት ሲሆን ይህም በገበያ በሚወሰነው የውጭ ምንዛሪ ተመን ምክንያት እዳውን በብር ሲሰላ በእጥፍ ስለሚጨምረው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእዳ አረንቋ ውስጥ መውደቋ ለአይ ኤም ኤፍ አሳሳቢ ነው፡፡ ዛምቢያ እ.ኤ.አ በ2020 ብድሯን መክፈል ተስኗት አጉራ ጠናኝ ማለቷን ተቋሙ አይረሳውም፡፡ ተቋሙ አሁን እየሰራ ያለው ኢትዮጵያም አንደ ዛምቢያ በብድር ጫናው ሳቢያ አልቻልኩም ብላ በዝረራ ከመውጠቷ በፊት እንደምን ደጋግፎ እስትንፋሷን በማቆየት እዳዋን ለአበዳሪዎቹ አንድትከፍል ማስቻል ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መረጃ የሀገሪቱ የዋጋ ንረት መቀነሱን ይፋ አድጓል፡፡ የዋጋ ንረቱ የቀነሰ የመሰለው ግን ባንኮች በሚሰጡት ብድር መጠን ላይ ገደብ በመጣሉና የብድር ወለድ ምጣኔውም በማደጉ ምክንያት ነው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ቀነሰ የሚለው ዜና ለአንዳንድ ወገኖች እንደ መልካም ዜና የሚቆጠር ቢሆንም የዚያኑ ያህል የመልካም ፖሊሲ ውጤት ከመሆኑ ይልቅ ኢኮኖሚው መጨነቁንና እንዳይላወስ ተጠፍንጎ መያዙን የሚያመለክት ነው፡፡
አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የዋጋ ንረት ቀነሰ በሚለው መረጃ ላይ ወቅታዊ አዝማሚያ መሆኑን ከግምት በማስገባትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማተኮር የፈለገ ይመስላል፡፡ ሌሎች ኢኮኖሚስቶች ደግሞ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከምና ባንኮች የሚያበድሩትን የገንዘብ መጠን መገደብ ጊዚያዊ የዋጋ ንረትን ቅነሳ ቢያስከትልም እውነተኛ ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማገገም እንደማያስገኝ ይሞግታሉ፡፡ ይልቁንም ባንኮች በሚያበድሩት ገንዘብ ላይ ገደብ መጣሉና በዚህም እርምጃ የዋጋ ንረቱ ቢቀንስ እንኳ የኢኮኖሚው መኮማተር የማይቀር አሉታዊ ውጤት ሆኖ ይከሰታል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን ብድር አግዳና የቢዝንስ ፍላጎቶችን ገድባ ኢኮኖሚው ሳይንኮታኮት እስከ መቼ ትዘልቃለች የሚለው ነው፡፡
የአይ ኤም ኤፍ እና የኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎች በነጻ ገበያ ተአምር የሚያምኑ ይመስላሉ፡፡ በውጭ ምንዛሪ ላይ የወጡ ደንብና መመሪያዎችን ማንሳት፣ አንዳንድ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ሁሉ ማስወገድ፣ አስመጪዎች በውጭ ምንዛሪ ያገኙትን ገቢ ለራሳቸው እንዲጠቀሙበት መፍቀድና የመሳሰሉት የነጻ ገበያ የአሰራር ዘይቤዎች በገበያው ውስጥ ብዙ ዶላር እንዲዘዋወር በማድረግ የውጭ ምንዛውን እጥረት በመፍታት ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ ያደርጋል እያሉ ይደሰኩራሉ፡፡
እውነታው ግን ወዲህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምንጭ በደንብና መመሪያዎች ወይም በአሰራር ስልት ችግር የመጣ ሳይሆን የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግር ያስከተለው ነው፡፡ ለምሳሌ በደህናውም ጊዜ ቢሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው እንደ ቡናና የቅባት እህሎች ባሉ የግብረና ሸቀጦች ላይ በመሆኑ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት የሚመጥን አይደለም፡፡ እስካሁን ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የኢንዱስትሪና መሰል ምርቶችን መላክ የሚያስችል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ማድረግ አልቻለችም፡፡
ወደ ቅርብ ጊዜውና ሁለተኛው የአይ ኤም ኤፍ ግምገማ ስንመለስ ሁለት ጉዳዮችን አይቶ እነዳላየ አልፏቸዋል፡፡ አንደኛው ያለፉት ወራት የኢትጵያ የወርቅና የቡና የወጭ ንግድ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ዶላር ማስገኘቱን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የባንክ ብድር በከፍተኛ የወለድ መጠኑ ምክንያት ባለመወሰዱ የቀነሰውን የወጋ ንረት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች የሀገሪቱን የጥሬ ገንዘብ ቀውስ በመጠኑም ቢሆን እንዲቀንስ አግዘዋል፡፡ ተቋሙ ግን በሪፖርቱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏቸዋል፡፡ ተቋሙ ሁኔታውን ጆሮ ዳባ ልበስ ለማለት ምክንያት አለው፡፡ ምክንያቱም በተጠቀሱት ክንውኖች ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ መጨመሩና በባንክ ብድር ላይ ገደብ መቀመጡና የባንክ ወለድ መጨመሩ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ ማድረጉን መቀበል የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቀውስ ምንጭ የመጥፎ ፖሊሲ ችግር ሳይሆን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር መሆኑን መቀበል ስለሚሆንበት ነው፡፡
የአይ ኤም ኤፍን ዶግማ የማይቀበሉ ኢኮኖሚስቶች ለኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ከተቋሙ በተቃራኒ ምክረ ሀሳብ ይለግሳሉ፡፡ እነርሱም፡-
የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ደረጃ በደረጃ ማስተካከል፡ – ኢኮኖሚውን በሚያናውጥ መልኩ የብርን የመግዛት አቅም በአንድ ጀምበር ከማዳከም ይልቅ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ደረጃ በደረጃ ማስተካከል፡፡ ጉን ለጎንም የተለያዩ የንግድ ድርድሮችን በማድረግና የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን በማሳደግ የዋጋ ንረትን ማለዘብ፡፡
ስትራቴጂዊ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ማድረግ – አይ ኤም ኤፍ እንደሚሰብከው መንግስት ሁሉኑም ነገር ለገበያው ትቶ መውጣት ሳይሆን በተጠና ሁኔታ በወሳኝ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መግባት ነው ያለበት፡፡ በተለይም የውጭ ምንዛሪው በቁልፍ የኢንዱስትሪ ዘርፎችና ወሳኝ ምርቶችን ወደ ሀገር ማስገባት ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
በእዳ እፎይታና ሽግሽግ ረገድ ጠንክሮ መስራት – ኢትዮጵያ የእዳ እፎይታና ሽግሽግ እንድታገኝ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዛምቢያ፣ ጋናና ቻድ የእዳ እፎይታና ሽግሽግ ብትጠይቅ ምንም የሚያስነውር አይደለም፡፡
የወጪ ንግድን ማስፋትና ማጎልበት – ኢትዮጵያ በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ተመን ተግባራዊ በማድረግ የውጭ ምነዛሪ ችግሯን ማስወገድ አትችልም፡፡ ስለዚህም የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ የኢንዱስትሪ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግና የቴክኖሎጂ ምርቶችን ወደ ውጭ ልካ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበትን ስልት መንደፍ ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያ አይ ኤም ኤፍ በቀደደላት ቦይ መንጎድ ከቀጠለች መጨረሻዋ አያምርም፡፡ ተቋሙ በቀደደለቻው ቦይ የፈሰሱት ግብጽ፣ ዛምቢያና አርጀንቲና ምን እንደደረሰባቸው ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ተቋሙ በኢትዮጵያ ላይ አካሄድኩት ያለው ሁለተኛው ግምገማ የነገረን ተቋሙ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲል ፖሊሲ አውጪዎች ለሰሩት ጥፋት ደሀው የህብረተሰብ ክፍል እዳ ከፋይ መሆኑን ቁልጭ አድረጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ተቋሙ በግምገማው በአጭሩ የነገረን አበዳሪዎች ገንዘባቸውን ስለሚፈልጉ በወቅቱና በአግባቡ ክፈሉ፣ ኢትዮጵያ የአይ ኤም ኤፍን አስርቱ ትዕዛዛትን ሳትቀንስ ሳትጨምር ተግባራዊ ታድርግ፣ ድጎማ የሚባል ነገር አስወግዱ የሚሉና ከሀገሪቱ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣሙ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ቀጭን ትእዛዙን ነው ያስተላለፈው፡፡
እናስ ጎበዝ በእውነተኛ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢንዱስትሪዎቻችንን ገንብተን፣ ለችግር ተጋላጭ የሆነውን የህበረተሰባችንን ክፍል ደግፈን፣ ምርቶቻችንን አስፋፍተንና አጎልብተን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ሉአላዊነታችንን ማረጋገጥ ይሻለናል ወይስ ከአጋም እንደተጠጋ ቁልቋል ስናለቅስ መኖር ይሻለናል?