በአፋር ክልል ዱላሳ ወረዳ የሚገኘው ከሰም የስኳር ፋብሪካ፣ በክልሉ እየተከሰተ ባለው ለወራት የቀጠለ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ይፋ ባደረገ በወሩ፣ ከ3,700 በላይ ሠራተኞቹን ከሥራ ማሰናበቱ ታወቀ።
በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት ተፈናቅለው በካምፕ የተጠለሉ 3,750 ቋሚና ጊዜያዊ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች፣ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ባልጠበቁት ሁኔታ ከሥራ ተሰናብተዋል።
ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ 123 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው ከሰም ስኳር ፋብሪካ ከ10 ዓመት በፊት ነበር ስኳር ማምረት የጀመረው፡፡
በዓመት 260 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም የነበረው ይህ ስኳር ፋብሪካ በአዋሽ አካባቢ ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት ስራ አቁሟል፡፡
በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ፋብሪካው ከአዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች እየተደጋገሙ ሲሆን እስካሁን በመንግስት ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች ላይ የተወሰኑ ጉዳቶችን ከማድረስ የዘለለ ከባድ ጉዳት አላደረሱም፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ ከ30 ጊዜ በላይ በአፋር ክልል አዋሽ ከተማ አቅራቢያ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከ60 ዓመት በኋላ ከፍተኛ የተባለ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟል፡፡
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 8 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟል፡፡
በዚህ አደጋ ምክንያት በአፋር ክልል ባሉ መኖሪያ ቤቶች እና የመንግስት ተቋማት ላይ አነስተኛ ጉዳት ያጋጠመ ሲሆን ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ ተሰምቷል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው ማስታወቂያ የርዕደ መሬቱ ማዕከል ከሆኑ 12 ቀበሌዎች 85 ሺህ ዜጎችን ሊፈጠር ከሚችለው አደጋ ለመጠበቅ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዘዋውረዋል፡፡
በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ማዕከላቸውን አድርገው የተለያየ መጠን ያላቸው የርዕደ መሬት ክሥተቶች በተደጋጋሚ መከሠታቸውን ተቋሙ አስታውቋል።
ክሥተቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እያደጉ ይገኛሉ ያለው ተቋሙ በተለይም በዚህ ሳምንት በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ 5.3 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ መንቀጥቀጥ መከሠቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
መንግሥት ክሥተቶቹን በዘርፉ ባለሞያዎች በቅርብ እየተከታተለ መሆኑንም አስታውቋል።
በተጨማሪም በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል (epicenter) የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ መንግሥት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቦታው ተሰማርተው የጉዳቱን መጠን ከገመገሙ በኋላ ለተጎጂዎች የተለያዩ እርምጃዎች በወሰድ ላይ ናቸው ተብሏል።
በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማሥፈር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው።
በተጨማሪም ርዕደቱ በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በኢኮኖሚ ተቋማት እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ በመከታተል ላይ እንደሚገኝም መንግስት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የመሬት መንቀጥቀጡ በዋና ዋና ከተሞች የጎላ ተጽዕኖ ያላደረሰ ቢሆንም ዜጎች በባለሞያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩም መንግስት አሳስቧል።