ኢትዮጵያ በዓመት 400 ሺህ ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ እየላከች ነው ተባለ

ኢትዮጵያ በሰለጠነ የሰው ሀይል ዕጥረት ምክንያት ሰራተኞችን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ እንዳልቻለች ተገለጸ

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በዘረጋው የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ገበያ ላይ ሂዶ ለመስራት ከሀገራት ከሚቀርበው ጥያቄ አንፃር፤ በከፍተኛ ሁኔታ የሚላኩ ዜጎች እጥረት መኖሩን ገልጿል፡፡

ከመዳረሻ ሀገራት በኩል በርካታ የሰለጠነ የሰው ሀይል ጥያቄን ለኢትዮጵያ እንደሚቀርብ የገለጹት፤ በሚኒስቴሩ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊ ብርሀኑ አለቃ ናቸው፡፡

በብዛት የሰው ሀይል ጥያቄ ያለባቸው ሀገራት በሙሉ ከኢትዮጵያ ሰው ለመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸውም ሀላፊው አንስተዋል።

ጥያቄ ከሚያቀርቡ ሀገራት መካከልም ከመካከለኛው ምስራቅ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ እና ጆርዳን ናቸው።

እንዲሁም ከአውሮፓ ሀገራት ደግሞ ጀርመን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና ፖላንድ በከፍተኛ ሁኔታ ከኢትዮጵያ የሰለጠነ የሰው ሀይል የሚፈልጉ ሀገራት መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እነዚህ ሀገራትም በጥቅሉ በሚሊዮን የሚቆጠር የሰው ሀይል ጥያቄን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በዓመት ከ50 ሺሕ ያልበለጠ የሰው ሀይል ወደ ውጪ ሀገራት ይላክ እንደነበር ያነሱት ኃላፊው፤ “አሁን ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በመጣው ለውጥ አማካኝነት በትንሹ እስከ 400 ሺሕ ሰው ይላካል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ሀገራት ከሚያቀርቡት ቁጥር አንፃር ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ስለመኖሩ ተናግረዋል።

በዚህም ሰዎችን ለሥራ ከማሰማራት አኳያ ብቻም ሳይሆን፤ ኢትዮጵያም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ስለዚህም ማንኛውም ሰው በየሙያው ሰልጥኖ ተገቢውን የምዘና ፈተና በመውሰድ፣ የሥራና ክህሎት በሚያዘጋጀው የሥራ ገበያ አሰራር  ላይ በመመዝገብ እና በየቀበሌው ባሉት የመረጃ መቀበያ ጣቢያዎች አስፈላጊ መረጃዎችን በመሙላት የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *