ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሀይሉን ባልሆነ ቦታ እያባከነ ይሆን?

የኢትዮጵያ ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግና ከዚህ በፊት ይነሱ  የነበሩ ትርክቶች መቋጫ እንዲያገኙ በሚል ነበር በ2014 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሞ ስራ የጀመረው፡፡

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቶ የአጀንዳ መለየትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም በመስራት ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ በሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ደቡብ ምዕራብ ፣ ኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አጀንዳዎችን መለየቱን አስታውቋል፡፡

ይህን ተከትሎ ኢትዮ ነጋሪ የሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ክፍሎች በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ያላቸውን ዕምነት እና በኮሚሽኑ በአጀንዳነት እንዲካተት ስለሚፈልጓቸው ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡

የ19 ዓመቷ ተማሪ ምህረት ከበደ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ስትሆን ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ እንዳስደሰታት ነግራናለች፡፡ “በኢትዮጵያ በተፈጠሩ የፖለቲካ ችግሮች ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰን መስራት አልቻልንም፡፡ የፖለቲካ ችግሮች ባለመፈታታቸው ምክንያት የስራ እድል መፍጠር አልተቻለም የምክክር ኮሚሽኑ ለዚህ ችግር መፍትሔ ያመጣል ብዬ እጠብቃለሁ” ብላናለች፡፡

ሌላኛው የይርጋለም ከተማ ነዋሪ አለማየሁ ደምሴ በበኩሉ ወጣቱ ወደፈለገው አካባቢ ተንቀሳቅሶ እንዲሰራ እድል ይፈጥራል ምክክር ኮሚሽኑ፣ እንደ ሀገር የተሻለ ሰላም ይኖረናል ሲል ኮሚሽኑ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተናግሯል፡፡

“በኢትዮጵያ በተፈጠሩ የፖለቲካ መካረር ምክንያቶች ጦርነት እና የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴዎች ተስፋፍተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በየጊዜው ወደ ውትድርና ማሰልጠኛዎች የሚገቡ ወጣቶች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ልዩነቶች በምክክር መፍታት ከተቻለ ወጣቶች ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ወደሚለውጡ ስራዎች ያዘነብላሉ” ሲልም አክሏል አለማየሁ፡፡

በኢትዮጵያ ሲዳማን ጨምሮ ሰላምን የሚጠላ ማህበረሰብ አለ ብዬ አላስብም፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ ሁከቶች የተጎዱ ቤተሰቦች አሉኝ ንብረታቸው ወድሟል፣ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለነዚህ ሁሉ ጉዳቶች ካሳ እሚያገኙበትን ስርዓት ይፈጥራል ብሎ እንደሚያስብም ተናግሯል፡፡

የዩንቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት በጉዞ ላይ እያለሁ ከሁለት ዓመት በፊት ጓደኞቼ ባልታወቁ ታጣቂዎች ታግተዋል፡፡ እስካሁን እነዚህ ታጋቾች አልተለቀቁም፡፡ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ለዚህ እና መሰል ችግሮች መፍትሔ ያመጣል፡፡ በብሄር መደራጀት ሊከለከል ይገባል ሲልም አክሏል፡፡

የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ለማ ኦያቴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ እንደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አይነት ተቋማት እንዲመሰረቱ ሲጠይቁ ከነበሩ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ በሐዋሳ ባካሄደው የአጀንዳ ልየታ ስብሰባ ላይ ብልጽግና ፓርቲ ከሌሎች በተለየ መልኩ እየተሳተፈ ነበር የሚሉት አቶ ለማ ምንም ቢሆን ግን ኮሚሽኑ በሲዳማ እየሰራው ያለው ስራ ጥሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሲዳማ እንደ ሀገር የሰንደቅ አላማ፣ የስራ ቋንቋ ጉዳይ፣ በሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲሁም በፓርቲ እና መንግስት መካከል ያለው የመቀላቀል ሁኔታ እንዲስተካከል እንፈልጋለን ሲሉም አቶ ለማ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የትጥቅ ትግል ያነሱ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ያገኛሉ ብለን ስለምንጠብቅ ፓርቲያችን ለሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን ድጋፍ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ከሁሉም የሲዳማ ሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በተገኙበት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አወያይነት ተወያይተናል የሚሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ወሰንየለህ ሰምኦን ናቸው፡፡

አቶ ወሰንየለህ አክለውም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ቢፈታልን ብለን ያነሳናቸውን ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አራት ጊዜ የነበሩ የመንግስት ለውጦችን በሚገባ ሳንጠቀምባቸው አልፈዋል፡፡ አሁን የመጣው አጋጣሚ ጥሩ ነው፡፡ ከችግሮቻችን የምንወጣበት አጋጣሚ አሁን መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም አካል አጀንዳዎቻችን እነዚህ ናቸው እያሉ እያስቀመጡ ነው፡፡ ለዘመናት ሲያጋጩን የነበሩት ችግሮች ይፈታሉ ብዬ እጠብቃለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በሐዋሳ ዩንቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አሊ አወል በበኩላቸው ብሔራዊ ምክክር በህዝብ እና መንግስት መካከል መቃቃር ሲኖር የሚደረግ መሆኑን፣ ሀገርንም ወደ ዘላቂ ሰላም እና እድገት የሚመልስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሐገራዊ ምክክርን ከኢትዮጵያ በፊት የሞከሩት በርካታ ሀገራት ነበሩ የሚሉት መምህር አሊ ነገር ግን ወጤታማ የሆኑም ያልሆኑም ሀገራት እንዳሉም አክለዋል፡፡ በኢትዮጵያም ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም እና ችግሮች መፈታት አለባቸው የሚለው ፍላጎት ከሕዝብ እና ከመንግስት በመምጣቱ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ መምህር አሊ አስተያየት ከሆነ በሲዳማ ክልል ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎች እየተሰበሰቡ ቢሆንም እስካሁን የተነሱት አጀንዳዎች ግን መፈተሽ አለባቸው፡፡ አጀንዳዎቹ ሰፋ ያሉ እና ብሔራዊ ሊሆኑም ይገባል፡፡

የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ስንመለከት ብዙ ጊዜ ብሔራዊ ምክክር ከብሔራዊ ቀውስ በኋላ የሚካሄድ ነው የሚሉት መምህሩ “በኢትዮጵያ ያለውን ስናይ ከፍተኛ ተቃርኖ እና ብሔራዊ አደጋ የሚደቅኑ ችግሮች ባለባቸው ክልሎች ላይ በተገቢው መንገድ አጀንዳ እየተሰበሰበ እና ውይይት እየተካሄደ አይደለም፡፡ ምክክር ኮሚሽኑ ብዙ ችግር በሌለባቸው አካባዎች ላይ ነው በስፋት አጀንዳ እየሰበሰበ ያለው፡፡ ህዝብ ስለተሰበሰበ እና አጀንዳ ተሰብስቧል ስለተባለ ብቻ ችግር ይፈታል ማለት አይቻልም” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን ችግር የማይፈታ፣ በሱዳን፣ደቡብ ሱዳን እና የመን የከሸፈው አይነት ምክክር እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኬንያ ከ12 ዓመት በፊት ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ የገጠማትን የፖለቲካ ቀውስ በእውነተኛ ምክክር አስተካክላለች፡፡ ይህ ምክክር አሁን ላይ ኬንያ ከምስራቅ አፍሪካ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እና ሀገር እንዲኖራት አድርጓል፡፡ ይህ የተፈጠረው እውነተኛ እና ትክክለኛ አሳታፊ ውይይት በማድረጋቸው እንደሆነም መምህር አሊ ተናግረዋል፡፡

በሱዳን የነበረው ምክክር ሳይሳካ እና ወደ እርስበርስ ጦርነት ያመራው የምክክር አጀንዳው ከቤተ መንግስት ይመጣ ስለነበር ነው የሚሉት መምህር አሊ ብሔራዊ ምክክር ከውጭ ጣልቃ ገብነት የጸዳ፣ ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ተሳታፊዎች ያሉበት፣ የሀገሪቱን ሁኔታን ከግምት ውስጥ ባስገባ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ መካሄድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ስናየው ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አብዛኛውን ጊዜ እና ጉልበቱን እያባካነ ያለው ዋነኛ እና አስከፊ ችግር ባለባቸው ክልሎች እንደ አማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ አለመሆኑ ምክክሩ ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርገው እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን በበኩሉ እስካሁን በሰባት ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳድሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎቹን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በሰጡት መግለጫ ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በቀሪዎቹ አካባቢዎች አጀንዳ የማሰባሰብ ስራው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋነኛ የጸጥታ እና የፖለቲካ ችግር ካለባቸው ክልሎች መካከል የሚጠቀሱት አማራ እና ትግራይ ክልሎች አጀንዳዎችን ለማሰባሰብ ስራዎች መጀመራቸውን የሚናገሩት ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ የሕብረተሰብ ተወካዮችን እየመለመሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ሐገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን ለመስራትም ከጊዜያዊ አስተዳድሩ እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያየ መሆኑን፣ ምክክሩ ቢጀመር ይጠቅመናል ብለው እንደሚያስቡ እነዚሁ አካላት እንደነገሯቸውም ፕሮፌሰር መስፍን አክለዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *