አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ አማራ ክልል እየተፈጸመ ነው ያለውን የጅምላ እስራት ለማስቆም አስቸኳይ አለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ የሀገሪቱ መንግስት በክልሉ ሰፊ የእስር ዘመቻ ከጀመረበት መስከረም 2024 ጀምሮ አራት ወራት መቆጠራቸውን አመላክቷል፡፡
አምነስቲ ባወጣው መግለጫ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 28 ቀን 2024 የኢትዮጵያ ፌዴራል እና የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ወደ አራት የጅምላ እስር ቤቶች በማጓጓዝ በክልሉ ውስጥ ማሰራቸውን ገልጿል።
እስር ከተፈጸመባቸው መካከል ዳኞች፣ አቃቤ ህጎች፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራንን ጨምሮ የፍትህ አካላት ይገኙበታል ተብሏል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ማነስ ተችተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ “በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘፈቀደ ሲታሰሩ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ዝምታን መምረጡ አሳፋሪ ነው፤ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ከአፍሪካ እና ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አካላት ጋር በመሆን በግፍ የታሰሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሊጠይቁ ይገባል” ብለዋል፡፡
ቻጉታህ አክለውም “በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያለምንም ክስ እና ፍርድ ቤት ለወራት አስሮ ማቆየት አይን ያወጣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፤ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በዘፈቀደ የታሰሩትን ግለሰቦች በሙሉ በአስቸኳይ መፍታት ወይም አለም አቀፍ እውቅና ባላቸው ወንጀሎች መክሰስ አለባቸው” ብለዋል።
በቅርብ ወራት ውስጥ አራት የፍትህ አካላት በጥቅምት 2024 ተፈተዋል እንዲሁም ሶስት ዳኞች፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ስር የሰደደ የጤና ችግር ያለባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር ቢለቀቁም አሁንም በሺዎች የሚቆየሩ ሰዎች ያለ ክስ እና ፍርድ በእስር ላይ እንደሚገኙ መግለጫው አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመስከረም ወር አጋማሽ እስከ ታህሳስ ወር 2017 እንደሚሸፍን በገለጸውና ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርቱ በአማራ ክልል 6 ሺ ሰዎች ለዘፈቀደ እስር ተዳርገዋል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ በሶስት ወራት ውስጥ 120 ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ በዚሁ ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
ኢሰመኮ እንደገለጸው ዳንግላ፣ ጭልጋ፣ ኮምቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ዜጎች ከህግ ውጭ በጅምላ ታሰረው የሚገኙባቸው ቦታዎች ናቸው።
ሪፖርቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ እንደማይሸፍን የገለጸው ኢሰመኮ ግድያዎቹ በአብዛኛዎቹ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መፈጸማቸውን ጠቅሷል።