የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አንዳስታወቀው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁን በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ተጎድተዋል።
ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ቢሮው ጠቅሷል።
በአጠቃላይ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አገልግሎት ለመመለስ 112 ቢሊየን ብር ያስፈልጋልም ተብሏል።
ቢሮው ባስጠናው ጥናት መሠረት ይህ ገንዘብ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባትና መጠገን በተጨማሪ ተጓዳኝ የትምህርት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ነው፡፡
የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ ካለበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት እና ፋኖ ታጣቂዎች የተጀመረው ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ውጪ እንደሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል ያደረገውን የሶስት ወራት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ሪፖርቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሙሉ የሚሸፍን አይደለም ያለው ኮሚሽኑ በእነዚህ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የተሟላ ክትትልና ምርመራ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ውጤታማ ክትትልና ምርመራ የተከናወነባቸውን ጉዳዮች ብቻ በማሳያነት እንዳቀረበም ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከልም ከፍርድ ውጭ ግድያ መፈጸም፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል እና የዳኝነት ነጻነት መሸርሸሮች እንዳሉም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
በአማራ ክልል በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ120 በላይ ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ የገለጸው ኢሰመኮ ግድያው በአብዛኛው በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸመ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ እንደፈጸሙ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ፋኖ ናችሁ እና ለፋኖ ትረዳላችሁ በማለት ንጹሃንን ሲገድሉ የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ የመንግስት አገልጋዮች ናችሁ በሚል ግድያውን ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ፣ ኢጋድ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም እና ተፋላሚዎች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ በተደጋጋሚ አሳስበዋል።