የሶማሌላንድ የገንዘብ እና ልማት ሚኒስቴር ዛሬ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ የኢትዮጵያ ትራንዚት ማሳለጫ ቢሮዎች ስራ መጀመራቸውን ገልጿል።
የሶማሌላንድ የንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አብዲረሺድ ኢብራሂም ደግሞ “የሶማሌላንድ መንግሥት በበርበራ ወደብ የኢትዮጵያ ትራንዚት ማሳለጫ ቢሮዎችን ስራ አስጀምሯል ” ሲል ይፋ አድርገዋል።
“ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ውጥን ቀጠናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር ሶማሌላንድ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ አክለዋል።
ቢሮው በወደቡ የሚራገፉ ጭነቶችን ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ መዳረሻዎች እንዲጓጓዙ የሚያሳልጥ ነውም ተብሏል።
በርበራ ወደብ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትሱ DP World ይተዳደራል የተባለ ሲሆን የበርበራ ወብ ዋና ስራ አስፈፃሚ ስፓቺ ዋታንቫራቺ ተገኝተው እንደነበር ገልጿል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው “ይህ ቢሮ ወደቡ ላይ የሚራገፉ የተለያዩ ጭነቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓጓዙ የሚያሳልጥ ነው ” ብለዋል።
የሶማሌላንድ የገንዘብ እና ልማት ሚኒስትሩ ሳድ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ግንኙነታቸው የተጠናከረ ነው ፤ 120 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ትችላለች ” ማለታቸው ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላድ ጋር የወደብ ስምምነት የተፈራረመችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር፡፡
ከዚህ ስምምነት በኋላ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት የሻከረ ሲሆን ኢጋድ፣ ቱርክ እና ሌሎች ሀገራት እና ተቋማት ሁለቱን ሀገራት ለማስማማት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነትን በይፋ ካልሰረዘች ግንኙነቴን አላድስም በሚል በአቋሟ እንደጸናች ነች፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በዲፕሎማሲ ውጥረት ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች በቱርክ አንካራ ተገናኝተው ሊመክሩ መሆኑ ተነገረ፡፡
አዲስ አበባ ከራስገዟ ሶማሊላንድ ጋር በባለፈው አመት መጀመርያ የወደብ የመግባብያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ የጎረቤታሞቹ ሀገራት ግንኙነት ሻክሯል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስለ ውይይቱ እስካሁን የተሰጠ ማረጋገጫ ባይኖርም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ቱርክ የሚያቀኑ ከሆነ ሁለቱ መሪዎች ለአመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ በዛሬው እለት ለመጀመርያ ጊዜ በቱርክ አንካራ ፊት ለፊት ይገናኛሉ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ በተዘጋጀው ሶስተኛው ዙር ድርድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ቱርክ አንካራ በማቅናት ላይ መሆናቸውን የሃገሪቱ የዜና ወኪል በትላንትናው ዕለት ዘግቧል።
የአሜሪካ ድምጽ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው የመሪዎቹ ውይይት የሚደረገው በኢትዮጵያ ጥያቄ አቅራቢነት ነው፡፡