ለአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ምርጫ ሶስት ዕጩዎች ይፋ ሆኑ

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት የህብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ መሃማት ስልጣን ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት ቀርቶታል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ባሳለፍነው ነሀሴ ባወጣው ማስታወቂያ የህብረቱ አባል ሀገራት እጩዎች እንዲመዘገቡ በጠየቀው መሰረት ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ማዳጋስካር እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ዕጩ አቅርበው ጸድቆላቸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የኬንያ ፕሬዝዳንት ለመሆን አራት ጊዜ ተወዳድረው የተሸነፉት ራይላ ኦዲንጋ በይፋ የህብረቱ ሊቀመንበር ምርጫ ተወዳዳሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ሆነዋል፡፡

የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የራይላ ኦዲንጋ ጥያቄን በአዲስ አበባ በይፋ ያስተዋወቀ ሲሆን የምረጡኝ ቅስቀሳውን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከኬንያ በተጨማሪም የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀሙድ አሊ የሱፍ እና የቀድሞ የማዳጋስካር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ የራይላ ኦዲንጋ ተፎካካሪ ሆነዋል፡፡

እነዚህ እጩዎች የፊታችን ረቡዕ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ ህብረቱ በድረገጹ አስታውቋል፡፡

ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ቦታ ከቀረቡ እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል ራይላ ኦዲንጋ የተሻለ ድምጽ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡

እጩዎች ከተመዘገቡ በኋላ ኢትዮጵያዊቷ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጅት ስነጊዮርጊስ አባል የሆኑበት የአፍሪካ ህብረት የባለሙያዎች ቡድን እጩዎችን ገምግሞ ለመጨረሻ ዙር ምርጫ ድምጽ እንዲሰጥባቸው ይመራል፡፡

በባለሙያዎች ውሳኔ መሰረትም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች በሚስጥር በሚዘጋጅ ምርጫ ድምጽ የሚሰጡ ይሆናል፡፡

ምርጫው የፊታችን የካቲት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ወቅት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *