የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ተሳትፎ ከነበራቸው 274 ሺህ የትግራይ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንደሚመልስ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ውስጥም በመጀመሪያው ምዕራፍ 75ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ የማድረግ ስራውን በነገው እለት በይፋ እንደሚጀመር ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች በመቅረጽ ከሰባት ክልሎች ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከ760 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በሁለት ዓመታት ውስጥ የዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ስራውን ለመጨረስ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል።
ህዳር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮም ለመጀመሪያው ዙር ተዋጊዎች ብተና ማስፈጸሚያ ሀብት መንግስትና ከለጋሾች ማግኘት ተችሏል ተብሏል፡፡
መንግስት ኮሚሽኑ ስራ ሲጀምር 1 ቢሊዮን ብር የተለገሰ ሲሆን በተጨማሪም ከ7 ሀገራት 60 ሚሊየን ዶላር መገኘቱ ተገልጿል።
በድጋፍ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት የገንዘብ እና የቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ሲገለጽ 12 የሚጠጉ ሀገራት ደግሞ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ስራው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር እና ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር በመሆን የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎችን መለየት የተቻለ ሲሆን ሶስት ማዕከላትንም በመለየት የመረከብና የመጠገን ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
መቀሌ ፣ እዳጋ ሀሙስ እና አድዋ የመጀመሪያ ዙር ተዋጊዎች ስልጣና የሚወስዱባቸው አካባቢዎች ናቸው ተብሏል።
በመጀመሪያ ዙር ወደ ስልጠና ካምፖች የሚገቡ 75 ሺህ ታጣቂዎች በአራት ወራት ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን ኮሚሽኑ ገልጿል።
የተሃድሶ ስልጠና ሰነዶች ዝግጅትና የአሰልጣኞች ስልጠና፤ የመመዝገቢያ ሶፍትዌር ማበልጸግ የማዕከላት ርክክብና ጥገና እንዲሁም አስፈላጊ የሎጅስቲክስ ግጞዥና አቅርቦት ተካሂዷልም ተብሏል፡፡
በዚህ መሰረት የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ወደ ማዕከላት ሲገቡ የስድስት ቀናት የተሃድሶ ቆይታ ይኖራቸዋል።
በቆይታቸውም የዲጅታል ምዝገባና ማረጋገጥ፣ የስነ ልቦና እና የተሃድሶ ስልጠና ይወስዳሉ ተብሏል፡፡
የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ ለመሠረታዊ ፍጆታ እንዳይቸገሩ የመልሶ ማቀላቀል ክፍያ ተሰጥቷቸው ወደ ማህበረሰቡ እንደሚሸኙም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ በጀት በማሰባሰብ ለይ ስትሆን የአውሮፓ ህብረት 12 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡
የብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ከአንድ ወር በፊት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት 16 ሚሊዮን ፓውንዱ የትግራይ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡