በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት ባለስልጣንን ጨምሮ ከ60 በላይ ሰዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ ወረዳዎች ውስጥ በመንግስት የጸጽታ ሀይሎች እና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል

ውጊያ ከሚካሄድባቸው ወረዳዎች መካከል አንዱ በሆነው ደራ ወረዳ በትናንትናው ዕለት  ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ባለስልጣንን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል፡፡

ከተገደሉት መካከል የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ኮሩን አንዱ ሲሆኑ ከአስተዳዳሪው በተጨማሪም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ንጹሃን ዜጎችም ገኙበታል ተብሏል፡፡

የአመራሩ ግድያ የተፈጸመው አመራሩና በርካታ የጸጥታ ሃይሎች መንግስት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ሃይል ወደሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሲያመሩ ነው ተብሏል።

በደራ ወረዳ ገንዶ መስቀል አካባቢ ላለፉት ሶስት ሳምንታት የመከላከያ ሰራዊትን፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን (ወይም መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለውን) እና የፋኖ ሀይሎችን ባሳተፈው በዚህ ደም አፋሳሽ ግጭት በርካታ ንፁሀንን ጨምሮ የተፋላሚዎችን ህይወት አልፏል።

ባሳለፍነው እሮብ ብቻ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና በፋኖ ሀይሎች መሀል በነበረ ግጭት 47 ተፋላሚዎች ከሁለቱም ወገን እንደሞተ የታወቀ ሲሆን 5 ንፁሀንም ተገድለዋል ተብሏል።

በተጨማሪም በወረ፣ ጎላም፣ ግራኝ ሙቀጫ እና ቢርጄ መንደሮች ያሉ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይህን ግጭት ተከትሎ ነዋሪዎች አካባቢውን እና መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው እየተሰደዱ ባለበት ወቅት በታጣቂዎች የታገቱ እንዳሉም ተገልጿል፡፡

11 ቤተሰቦቼ ታግተውብኛል ያሉ አንድ ግለሰብ በሰጡን መረጃ እንዲለቀቁ 5 ሚልዮን ብር ክፈል እንደተባሉ ተናግረዋል።

ያለንን ገንዘብ አሰባስበን 500 ሺህ ብር ብንከፍልም እስካሁን ቤተሰቦቼ አልተለቀቁም” የሚሉት እኚህ ግለሰብ ተስፋ ቆርጫለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ ህዝብ የሚኖርባቸው ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የገቡ ሲሆን በርካታ የሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት የሰብዓዊ ድርጅቶች አለመግባባቱ በውይይት እንዲፈታ እየጠየቁ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተደጋጋሚ ባወጣው ሪፖርት ንጹሃን ለከፋ አደጋ መጋለጣቸውን ገልጾ ተፋላሚዎች ንጹሃንን ከጥቃት እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ብሪታንያ እና የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ያለው የንጹሃን እገታ፣ እስር፣ የጅምላ ግድያ እና ሌሎች ጉዳቶች እንዲቆሙ ጠይቀው ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *