የአማራ ዳኞች ማህበር የታሰሩ አባላቱ እንዲፈቱ ጠየቀ

የፌደራል መንግስት ክልል የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ በሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች አማካኝነት ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡

በክልሉ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ አዋጅ ከ10 ወራት በኋላ ያልተራዘመ ቢሆንም አሁንም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡

ከጦርነቱ ባለፈም በክልሉ ንጹሃን ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም የአማራ ዳኞች ማህበር እና ጤና ባለሙያዎች ማህበር አባላቶቻቸው ለተለያዩ ጉዳቶች መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር እንዳለው በክልሉ ያለው የደህንነት ችግር ዳኞች በነጻነት ስራቸውን እንዳይሰሩ እክል መፍጠሩን ገልጾ ባለፉት ቀናት ውስጥም 13 ዳኞች ታስረዋል፡፡

ከታሰሩት ውስጥ አራት ዳኞች ከእስር መለቀቃቸውን የተናገረው ማህበሩ ቀሪ እና በእስር ላይ ያሉ ዳኞች እንዲለቀቁም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች ማህበር በበኩሉ የጤና ባለሙያዎች በክልሉ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ለግድያ፣ እስር እና ለተለያዩ እንግልቶች መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡

“በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና አገልግሎት ባለሞያች የሞያ ነፃነት አጥተዋል” ያሉት የአማራ ክልል ጤና ባለሞያዎች ማኅበር ጸሀፊ “ባለሞያዎች የታጠቁ ኃይሎች በሚሰነዝሩት ጥቃት ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ” ማለታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል::

ከሁለት ሳምንት ወዲህ በምዕራብና ሰሜን ጎጃም ዞኖች የሚኖሩ ሁለት ፋርማሲስት ሲገደሉ በባሕር ዳር ከተማ አንዲት ነርስ በትላንትናው ዕለት ምሽት ላይ ሥራ ላይ እያለች ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተመትታ መቁሰሏን የማኅበሩ ጸሐፊ ተናግረዋል።

ለደህንነቱ በመስጋት ስሙም ኾነ የሚሠራበት የሕክምና ተቋም እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚኖር የሕክምና ባለሞያ መተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ ሁለት የሙያ አጋሮቹ እንዲሁም በጎንደር ከተማ የሚገኘው የአይራ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ‘ከፋኖ ጋር ግንኙነት አላችሁ” በሚል መታሰራቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች በአማራ ክልል ንጹሃን ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ እና ምሁራንን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታሰሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ከሰኔ ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ጦርነት ከ160 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

ግድያ ከተፈጸመባቸው ዜጎች መካከል የአዕምሮ ህመምተኞች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

ጎንደር፣ የጎጃም አካባቢዎች፣ ደብረሲና፣ አታዬ፣ ሸዋሮቢት እና ሌሎችም ቦታዎች ያሉ ሲሆን መረጃ ለፋኖ ትሰጣላችሁ፣ የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ ናችሁ እና ያለ ምንም ምክንያት ንጹሃን በመኖሪያ ቤታቸው፣ በቤተ ክርስቲያናት እና በጉዞ ለይ እያሉ እንደተገደሉም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ አማራ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜ በሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሱ እንደሚገኝ  ገልጿል፡፡

ጉባኤው በአማራ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኝውን ሁኔታ ባወጣበት ሪፖርቱ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ባለመወጣታቸው የመብት ጥሰቱ እንደቀጠለ ይገኛል ብሏል፡፡

በአማራ ክልል የተለያዩ ከፍተኛ የጦር መሳርያዎችን ጭምር በመጠቀም የሚካሄደው ግጭት ቀጥሏል ያለው ጉባኤው በዚህም የሰዎች ህይወት እያለፈ ፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ግጭቱ በንፁሃን ላይ እያደረሰ ከሚገኝው ሞትና የአካል ጉዳት ባለፈ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ የጤናና የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *