መዳን የማይችሉ ሰዎችን ህይወት ማቋረጥ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ለፓርላማ ቀረበ

መዳን የማይችሉ ሰዎችን ህይወት ማቋረጥ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት ባሳለፍነው ሳምንት የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ “የጤና አገልግሎት አስተዳደር አዋጅ” ተብሎ ቀርቧል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ በርካታ ከጤና ጋር የተያያዙ ስርዓቶች የቀረቡ ሲሆን በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ መውለድ ላልቻሉ ባለትዳሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ የህክምና አገልግሎት ስለሚያገኙበት መንገድ ያስረዳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አተነፋፈሳቸው በመሳሪያ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሥርዓት ስለሚቋረጥበት ሁኔታ የሚደነግግ ረቂቅ ህግም ለምክር ቤቱ ቀርቦለታል፡፡

የዚህ ረቂቅ ህግ አላማም የሃገሪቱን እድገት ለማሳለጥና የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በሚደረግ ጥረት የልማቱ አንቀሳቃሽ የሆነውን ሕዝብ ጤንነት በተሟላ ሁኔታ መጠበቅ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በዚህ ረቂቅ ህግ መሰረት በመሳሪያ ላይ ብቻ የተመሰረተ የአተነፋፈስ ስርዓትን ማቋረጥን የሚፈቅድ ሲሆን ይህም የሚቻለው የልብ እና የመተንፈሻ አካላት የአሰራር ሥርዓት መመለስ በማይቻልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል።

የዚህ ስርዓት አተገባበር መመሪያን በቀጣይ የጤና ሚኒስቴር እንደሚያወጣ የተገለጸ ሲሆን ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ በማይድን ህመም የሚሰቃዩ ዜጎችን ለመርዳት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በአፍሪካ እንዲህ አይነት ህግ ሲወጣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በምዕራባዊን ሀገራት መተግበር ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

የጤና ጥበቃ ከሰሞኑ በርካታ የጤና ህጎች ማሻሻያ ረቂቅ ህጎችን ለህዝብ ተወካች ምክር ቤት በማቅረብ ላይ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት የዘር ፍሬ ልገሳን የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ “የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ” በሚል ርዕስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

አስራ ሁለት ክፍሎች ያሉት ረቂቅ አዋጁ ስለ አጠቃላይ የጤና አገልግሎት፣ ስለ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ስለ ልዩ የጤና አገልግሎቶች፤ ስለ ጤና ዘርፍ የሰው ኃብት ልማት እና አስተዳደር፤ ስለ ጤና እና ጤና ነክ ተቋማት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ቁጥጥርን የሚመለከቱ 60 አንቀጾች አሉት።

ስለ ልዩ የጤና አገልግሎቶች የሚያወሳው የአዋጁ አራተኛ ክፍል ከዘረዘራቸው የጤና አገልግሎቶች መካከል አንዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ ሕክምና አገልግሎት ነው።

በዚህ ንዑስ ክፍል ሥር የተካተተው አንቀጽ “ፈቃድ የተሰጠው የጤና ተቋም በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ የሕክምና አገልገሎት ሊሰጥ ይችላል” ሲል ሕክምናው በሕግ መፈቀዱን ይደነግጋል።

“የዘርፍ ፍሬ ልገሳ… ከዚህ ቀደም በሕግ የተፈቀደ ተግባር ያልነበረ” መሆኑን የጠቆመው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፤ በዚህኛው ረቂቅ አዋጅ “ልገሳውን ማከናወን እንደሚቻል የሚደነግግ እና የሚከናወንበትን ሥርዓት የያዘ ዝርዝር ድንጋጌ” መካታቱን አብራርቷል።

ይህ በዚህ እንዳለ ግን ኩላሊት ከሞተ ሰው እንዲወሰድ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ከስድስት ዓመት በፊት የተዘጋጀ ቢሆንም እስካሁን መልስ እንዳላገኘ የኩላሊት ህመምተኞች ማህበር ተናግሯል፡፡

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ የኩላሊት ልገሳን ከቤተሰብ ውጭ እንዲለገስ የማይፈቅደው የኢትዮጵያ የጤና ህግ  እንዲሻሻል ቢጠየቅም መልስ አለማግኘቱ ችግር እንደሆነ ተነግሯል።

በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት የጤና ህጎች ረቂቅ አዋጅ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን ስለ ኩላሊት ልገሳ የሚያወራው ህግ ግን እስካሁን እንዳልቀረበ  በኩላሊት ተካሚዎች ማህበር በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ኩላሊት ከሞተ ሰው በቀዶ ህክምና ከበጎ ፈቃደኞች እንዲወሰድ የሚረዳ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ላለፉት ስድስት ዓመታት እየተጠየቀ ቢቀጠልም እስካሁን ተግባራዊ መሆን እንዳልተቻለም  አስታውቀዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *