የኢትዮጵያ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫን እንዲያጠቡ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ ስለሚፈጸሙ ክፍያዎች የማሻሻያ ፖሊሲ ይፋ አድርጓል::

ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በዚህም ባንኮች በየእለቱ በሚያወጡት የውጭ ምንዛሬ የዋጋ ተመን ላይ በመግዣ እና በመሸጫው መካከል ከ10 በላይ ልዩነት ሲታይበት ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫው፤ አዲሱ የምንዛሬ ተመን አሰራር ይፋ መሆኑን ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ ያሉ ሂደቶችን ሲከታተል መቆየቱን አስታውቋል።

ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

በመሆኑም የውጭ ምንዛሬ መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ በላይ መሆን እንደሌለበት ብሄራዊ ባንክ አሳስቧል።

ብሔራዊ ባንኩ ይህንን በተመለከተ ለንግድ ባንኮች በደብዳቤ ማሳወቁን የገለጸ ሲሆን አዲሱ መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ እንዲተገበርም ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በመግለጫው አክሎም፤ አሁንም ቢሆንም ባንኮች የምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በራሳቸውና ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ስምምነት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁሟል።

ንግድ ባንኮች የምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በተናጠል በየቀኑ ማሳወቃቸውን መቀጠል እንዳለባቸውም ነው ብሄራዊ ባንክ ያስታወቀው።

ባንኮች ከውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የሚጠይቋቸውን ኮሚሽኖች ከምንዛሬ መሸጫ ጋር ሳይሆን በተናጠል ለደንበኞቻቸው እንዲያሳውቁሞ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የብሄራዊ ባንክን ማሳሰቢያ ተከትሎ ባንኮች በዛሬው እለት እያወጡት ባለው የዋጋ ተመን ላይ የመሸጫ ዋጋ ላይ ከ10 ብር በላይ ቅናሽ እያደረጉ ነው።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለታዊ የአንድ ዶላር ዋጋ ዝርዝር መሸጫ ዋጋውን ከ123 ብር ወደ 115 ብር ዝቅ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ግብይትን በገበያ እንዲመራ ውሳኔ ያስተላለፈች ሲሆን የብር የመግዛት አቅም ከእጥፍ በላይ ቀንሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *