ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአንድ ዓመት ዝም ብለው መቆየታቸው ተናገሩ

ፕሬዝዳንቷ በX ወይም በቀድሞው ትዊተር ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሁፍ ላይ “ዝምታ ነው መልሴ” የሚል ጽሁፍ አጋርተዋል።

ለምን ዝም እንዳሉ በጽሁፋቸው ላይ ያልገለጹት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ” እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ቴዲ አፍሮ፣ አሊ ቢራ ፣ማህሙድ አክመድ … ድንቅ ድምጻዊያን መካከል ናቸው። ሲሉም አክለዋል።

ፕሬዝዳንቷ የማህሙድ አህመድ ዘፈንን በሚያስታውሰው “የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደሰው ሲገፋው፣ መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው” የሚለውን ግጥምም በጽሁፋቸው ላይ ጠቅሰው አጋርተዋል።

ዝምታን “ለአንድ ዓመት ሞከርኩት” ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ምን ደርሶባቸው እንደከፋቸው፣ ለምን እንደከፋቸው እና ለምን ዝም እንዳሉ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያጋሩት ጽሁፍ የግላቸው እንጂ የጽህፈት ቤቱ እንዳልሆነ ጠቅሷል።

ኢትዮ ቼክ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ ሰቦቃን አነጋግሮ እንደዘገበው የፕሬዝዳንቷ ጽሁፍ የግላቸው እንጂ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤቱን አይመለከትም ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ አምስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሾሙ አምስተኛ ዓመታቸው ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ36 ዓመት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመን ተክተው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ፈረንሳይ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ እና ሌሎችም ሀገራት በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ፕሬዝዳንቷ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በውይይት እንደሚፈታ ተናግረው ነበር፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሚቀጥለው ሳምንት የፌደራል ህግ አውጪ ምክር ቤቶችን በነግግር እንደሚከፍቱ ይጠበቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *