የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ወሰነ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ይፋ ተደርጓል።

ጉባዔው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ላይ ለማድረግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ በተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መቀየሩን የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጉባኤው አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርቦ በካፍ ተቀባይነት ማግኘቱን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል።

በዚህም መሰረት የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ በቀጣይ ጥቅምት ወር በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።

ካፍ ዛሬ በሰጠው የቅድመ ጠቅላላ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ የ2024 ቻን አፍሪካ ዋንጫ በሚቀጥለው የካቲት ወር በናይሮቢ ፣ ካምፓላ እና ዳሬ ሰላም እንደሚካሄድ አሳውቋል።

የ2024 ቻን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጥቅምት እና ታህሳስ ወር ውስጥ እንደሚካሄድ ተያይዞ ተገልጿል።

ኬንያ የ2027 የአፍሪካ ዋንጫን ከዩጋንዳ እና ታንዛኒያ ጋር በጥምረት እንደምታዘጋጅ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አመታት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ለማስተናገድ እየተዘጋጀች መሆኗን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫን እ.ኤ.አ በ2029 ወይም በ2031 ለማዘጋጀት እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለእቅዱ መሳካትም ቢያንስ ስድስት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ካፍ ከዚህ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ መስፈርቶችን በማስቀመጡ ኢትዮጵያ አንድም ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም እንዳይኖራት አድርጓል ሲሉም አቶ ቀጀላ መርዳሳ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የካፍን ደረጃ የሚመጥኑ ስታዲየሞች የሌላት በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዘም ላሉ ጊዜያት ከሀገሩ ዉጪ ለመጫወት ተገድዶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።

የዉድድሩ አዘጋጅ ሀገራት ቢያንስ ስድስት ስታዲየሞችን እንዲያዘጋጁ ካፍ ቢያዝም ኢትዮጵያ እስካሁን የካፍን ደረጃ ያሟላ ስታዲየም የሌላት ሲሆን ውድድሩን ለማዘጋጀት እያደረገች ስላለው ዝግጅት የተባለ ነገር የለም፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች አንድ ስታዲየም ያላት ቢህንም ከዚህ ውስጥ አንዱም የካፍን ደረጃ የማያሟላ ሲሆን በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው እና 62 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም እስካሁን ዋንጫውን አንድ ጊዜ ብቻ ማሸነፍ ችላለች፡፡

በ1962 የአፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀችው ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ተጫውታ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችላለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *