ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጤና እክል ምክንያት ከሃላፊነት የለቀቁት ዮሀንስ አያሌው ብሩ (ዶ/ር)፣ የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሸመዋል፡፡
የአማራ ባንክ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ እንዳጋራው ዩሀንስ አያሌው ከዛሬ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በዋና ስራ አስፈጻሚነት መሾማቸውን ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ታሪክ በሰባት ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ከሁለት ዓመት በፊት ስራ የጀመረው የአማራ ባንክ 138 ሺህ ባለ አክስዮኖች የመሰረቱት የግል ባንክም ነው፡፡
ዮሐንስ አያሌው በልማት ባንክ የስራ ዘመናቸው ባንኩ ከነበረበት ውስብስብ ችግርና ክስረት ወደ ተሻለ አቋም እንዲመለስ ማስቻላቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ዶክተር ዮሀንስ አያሌው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን በምክትል ገዥነት እና በዋና ኢኮኖሚስትነት አገልግለዋል።
በዚህም በገንዘብ ኢኮኖሚስትነታቸው ብዙዎች የሚያደንቋቸው ሲሆን ከአምስት አመት በፊት የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በቦርድ አባልነት አገልግለዋል፡፡
የቀድሞው የልማት ባንኩ ፕሬዝዳንት ሀይለኢየሱስ በቀለ ሲለቁ የተኩት ዮሃንስ የባንኩ ፕሬዝዳንት በመሆን ለአራት አመታት የባንኩን ፖሊሲ መርተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ዶክተር ዮሀንስ በፕሬዝዳንትነት መምራት ከመጀመራቸው በፊት ባንኩ የገባበት ችግር ይዘጋ አይዘጋ የሚል ክርክር ላይ የደረሰ እንደነበረ ይነሳል።
ለዚህም ማሳያው የባንኩ ያልተመለሰ የብድር ምጣኔ ለልማት ባንኮች ከተቀመጠው የ15 በመቶ ገደብ አልፎ 57 በመቶ መድረሱ እና እጅግ በከፋ ችግር ውስጥ በመግባቱ ነበር።
በገንዘብ ሲታይም የባንኩ ያልተመለሰ ወይንም የተበላሸ የብድር ምጣኔ 27 ቢሊየን ብር ነበር።
ሆኖም አሁን በጤና ምክንያት እንደለቀቁ የተናገሩት ዶክተር ዮሀንስ በርካታ ያልተመለሰ ብድር ያለባቸውን ፋብሪካዎች አንድም ባንኩ ራሱ እንዲያስተዳድራቸው በማድረግ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የካፒታል ችግር ያለባቸውን ባንኮች ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙ አድርገው ከችግር እንዲወጡ ማድረጋቸው በስኬት ይነሳላቸዋል፡፡
እንዲሁም ለአንዳንድ ፋብሪካዎች ደግሞ አጣማሪ በማፈላለግ እንዲቋቋሙ አድርገው በርካታ ፋብሪካዎችን ወደ ብድር ከፋይነት እንዲመለሱ አድርገዋል።
በዚህም የባንኩ ያልለመለሰ የብድር ምጣኔ ከ57 በመቶ ወርዶ ፤ ከሚፈቀድለት 15 በመቶ ዝቅ ብሎ አሁን ላይ 6 በመቶ ከመድረሱ ባለፈ በየዓመቱ ትርፋማ እንዲሆን እንዳደረጉ ተገልጿል፡፡