አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ ወንበር እንዲኖራት አሜሪካ ጠየቀች

አሜሪካ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡ 

በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በምክር ቤቱ አፍሪካ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች እና ትናንሽ የደሴት ሀገራት አንድ ተለዋዋጭ ወንበር እንዲያገኙ ግፊት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡  

ጀርመን፣ ህንድ እና ጃፓን በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው እየጠየቁ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡

አምባሳደሯ አፍሪካ ቋሚ ውክልና እንዲኖራት አሜሪካ እንደምትደግፍ ቢናገሩም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አሁን ላይ ከሚገኙት አምስት አባል ሀገራት ውጪ እንዲሰጥ ዋሽንግተን ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል፡፡  

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ከፍተኛ ስልጣን ባለው የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው መጠየቅ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ለበርካታ ጊዜያት በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ድርድር ቢደረገም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ሆኖም በቅርብ ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እያደረገ በሚገኘው ሪፎርም ውስጥ ይህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንደሚገባው የድርጅቱን ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝና አባል ሀገራት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

አለም እና የሀይል አሰላለፏ ምክር ቤቱ ከተመሰረተበት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በብዙ መንገድ ተቀይሯል የሚሉት የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ጉተሬዝ ምክር ቤቱ ይህን ለውጥ አካቶ መጓዝ እንደሚኖርበት እየሞገቱ ይገኛሉ፡፡

በፀጥታው ምክር ቤት የሚደረጉ ማንኛቸውም ለውጦች በመመስረቻ ቻርተሩ መሰረት የአባል ሀገራቱን ሁለት ሶስተኛ ድጋፍ እና የአምስቱን የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ይሁንታ ማግኝት ይኖርበታል፡፡

 በ1945 በተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ 11 የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ሲኖሩ በ1965 ወደ 15 ሀገራት አድጎ 5 ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ያላቸው ቋሚ አባላትን እና 10 በየሁለት አመቱ የሚለዋወጡ ሀገራትን በአባልነት ይዞ ዘልቋል፡፡

አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት ቤት በአለም አቀፋዊ ሰለም እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ትላልቅ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይታወቃል፡፡

የጦር መሳርያ እና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲሁም የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በሀገራት እንዲሰማሩ መፍቀድ ከሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ አፍሪካን ወክለው በጸጥታው ምክር ቤት መካተት እንደሚፈልጉ በተለያዩ ጊዜያት በይፋ ጠየቁ ሀገራት ናቸው፡፡

አፍሪካ ህብረት አህጉሪቱን ወክለው በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ወንበር የሚያገኙ ሀገራትን በአብላጫ ድምጽ ማጽደቅ የሚኖርበት ሲሆን ሀገራት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *