የዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ልማት፣ ሴቶች እና እኩልነት ሚኒስትር አኔሌሴ ዶድስ በኢትዮጵያ ጉብኘት አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሯ በአዲስ አበባ በነበራቸው የአንድ ቀን ጉብኝታቸው ከኢትዮያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ጋር እንደተወያዩ ተገልጿል፡፡
የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉብኝቱን አስመልክቶ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ ሀገሪቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ግጭቶች እንዳሳሰቡት አስታውቋል፡፡
መግለጫው አክሎም በሁለቱ ክልሎች ያሉ ግጭቶች ንጹሃን እየጎዱ ነው ያለ ሲሆን የግጭቱ ሁሉም ተሳታፊዎች አለመግባባቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ዩኬም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ደህንነት እና ኢኮኖሚ ድጋፍ ማድረግ እንደምትፈልግ ሚኒስትሯ ከአምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት መነሳቱም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ዩኬ የዓለም አቀፍ ልማት እኩልነት እና ሴቶች ሚኒስትርን ወደ ኢትዮያ የላከችው አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር አዲሱ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚኖራት የትብብር አጀንዳዎች ዙሪያ ለመምከር እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በምርጫ ስልጣን የያዙት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በሰብዓዊ መብት ድጋፍ፣ ድህነት ቅነሳ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
ሚኒስትሯ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለስጣናት በተጨማሪ ከአፍሪካ ህብረት ሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ ጋርም ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ከኮሚሽነሩ ጋር በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት በተለይም በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ሰላም ዙሪያ መወያየታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡