ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የነፍሰጡሮች ቁንጅና ውድድር አዘጋጀች

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የነፍሰጡሮች የቁንጅና ውድድር በመስከረም ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለፀ ።

ታዋቂ ኢቪንትስ ከጤና ሚኒስቴር እና ከብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ጋር በጋራ ያዘጋጀውን ውድድር በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የውድድሩ አላማ በሀገሪቱን በስፋት እየተስተዋለ ስለሚገኘው የእናቶችን በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ህይወት ማለፍን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑ ተገልጿል።

ነፍሰ ጡርነት ውበት መሆኑን ለሌሎች በማስገንዘብ እና የጤና ክትትል የማያደርጉ ነፍሰ ጡር እናቶችን ክትትላቸውን እንዲያደርጉ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ለማሳየት መሆኑም ተመላክቷል።

በዚህ የቁንጅና ውድድር 15 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ አሸናፊዎች እንደየደረጃቸው ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።

በውድድሩ ለመውለድ የተዘጋጁ ነፍሰ ጡሮች በዲዛይነሮች በተዘጋጁ ቅንጡ የነፍሰጡር አልባሳት ተውበው ይታያሉ ተብሏል።

በቁንጅና ውድድሩ ለይ የሚወዳደሩ እርጉዝ ሴቶች ባሎችም በሚጠየቁት የእርግዝና ነክ ጥያቄዎቸ አማካኝነት እየተዳኙ ተወዳድረው በርካታ ሽልማቶችን የሚያገኙበት መሆኑንም አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

ጤነኛ እና ፍቃደኛ የሆኑ ማንኛውም እናቶች መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል።

ውድድሩ መስከረም 11 ቀን 2017 “ንግስት የነፍሰጡር ቁንጅና ውድድር” በሚል እንደሚካሄድ ታውቋል።

በ2017 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 295,000 የሚሆኑ ሴቶች በእርግዝና እና ወሊድ ወቅት ህይወታቸው አልፏል።

ከዚህም ውስጥ 94% የሚገኙት እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ የሚከሰት ሲሆን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ብቻ 66% (196,000) የእናቶች ሞት ሲመዘገብ፣ በኢትዮጵያም  14,000 እናቶች በዚሁ ዐመት ሞተዋል።

የእናቶች ሞት ማለት በእርግዝና ጊዜ ወይም ከወሊድ በኋላ በመጀመሪያ 42 ቀናቶች ውስጥ ከእርግዝናው ጋር ተያይዘው በሚመጡ የጤና ችግሮች ወይም በእርግዝናው ምክንያት ሊባባሱ በሚችሉ እና በህክምና አገልግሎት ችግር የሚከሰቱ የሴት ልጅ ሞት ማለት ነው።

አብዛኛዎቹ የጤና ችግሮች በእርግዝና ወቅት የሚመጡ ሲሆኑ የቀሩት ከእርግዝና በፊት በነበሩ የጤና ችግሮች በእርግዝናው ምክንያት በመባባሳቸው የሚመጡ ናቸው።

ከባድ የደም መፍሰስ ፣ በእርግዝና ወቅት የደም ግፊት መጨመር ፣ ኢንፌክሽን ፣ ከባድ ምጥ እንዲሁም ከጤና ተቋም ውጪ መውለድ፣ ብቁ ባልሆኑ ባለሙያዎች እና በህክምና መሳርያ ያልታገዘ ውርጃ ለእናቶች ህይወት መትፋት ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ሄው ጥናት ያስረዳል፡፡

የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት ውሳኔን ማዘግየት ፣ ወደ ህክምና ተቋም ለመድረስ መዘግየት እና የጤና ተቋም ከደረሱ በኋላ አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ መዘግየት የእናቶችን ሞት የሚያባብሱ በመባል ይታወቃሉ።

የእናቶች ሞት መጠን በእናቶች የእድሜ ክልል የሚለያይ ሲሆን በ 10–14 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣት ልጃገረዶች በእርግዝና እና ወሊድ ምክንያት ከሌሎች የእድሜ ክልሎች በበለጠ ለሞት ይዳረጋሉ።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *