የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር ከአንድ ሳምንት በኋላ በላቲን አሜሪካዋ ፔሩ አዘጋጅነት ይካሄዳል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ተመርጠው የመጨረሻ ልምምድ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለውድድሩ ከመረጣቸው አትሌቶች መካከል የ17 አመቱ አትሌት ሰው መሆን ታሪኩ አንዱ ነው፡፡
ይህ አትሌት ባሳለፍነው እሁድ ነሀሴ 5 ቀን 2016 ዓም የከሰዓት በኋላ ልምምድ ለመስራት ወደ ጫካ ወጣ ብሎ ልምምዱን ጨርሶ እያቀዘቀዘ ባለበት ያልታሰበ ሰው ጥቃት አድርሶበታል ተብሏል፡፡
አትሌቱን አንድ ሰው ከቀረበው በኋላ ፓሊስ ነኝ በማለት ራሱን ካስተዋወቀው በኋላ እዚህ አካባቢ ቁማር የሚጫወቱ ታውቃለህ በማለት ሲጠይቀው አላውቅም ብሎ እንደመለሰ ነገር ግን ወዲያው በፎጥነት ይህ ሰው አንገቱን ሲይዘው አትሌቱም እራሱን ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ ሌሎች ሁለት ሰዎች በድንገት በመምጣት በድንጋይ ጭንቅላቱን በመምታት አልወድቅ ሲል በሽጉጥ አይኑን ላይ ተኩሰው እንደመቱት አትሌቱ ለኢትዮ ራነርስ ተናግሯል፡፡
በአትሌቱ ላይ ጉዳት ያደረሱት ሰዎች ከመቱት በኋላ በኪሱ ውስጥ ይዞት የነበረውን ሞባይል በመውስድ እንደተሰወሩ ጓደኛቹ ገልፀዋል።
አትሌቱ በደረሰበት ጉዳት የአንድ አይኑ እይታ ሙሉ ለሙሉ እንዳቆመም ተገልጿል፡፡
አትሌቱ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተለ ሲሆን የፌደረሽን ሰዎች እየመጡም እየጠየቁት እንደሆነ ለህክምና የሚወጣውን የወጭ ደረሰኝ ያዙ ማንኛውንም ወጪ እንሸፍናለን በማለት በቃል እንደነገሯቸውም ጓደኞቹ ተናግረዋል።
ፖሊስ ስለ ጉዳዩ እውቅና አለው የተባለ ሲሆን ወንጀሉን የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን በመፈለግ ለይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን እስካሁን ተጠርጣሪ መያዙ አልታወቀም፡፡
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ውጤታማ ሀገር ብትሆንም በርካታ አትሌቶች ግን ልምምድ የሚደርጉበት ሜዳ እጥረት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
አትሌቶች አመቺ የልምምድ ቦታ ባለማግኘታቸው ምክንትም ራሳቸውን ለጉዳት እያጋለጡ ከተሽከርካሪዎች እና ዘራፊዎች ጋር እየታገሉ ሲሰሩ ትራፊክ አደጋን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳቶች እየተጋለጡ ናቸው፡፡