ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ በአንድ ወር ውስጥ ለሽያጭ ካቀረበችው ቡና በአዲሱ የ2017 በጀት አመት ሀምሌ ወር ከፍተኛ ገቢ ማግኘቷ ተሰምቷል፡፡
በ2017 በጀት አመት ሀምሌ ወር ከቡና ሽያጭ ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳህለማርያም ገብረ መድህን እንደተናገሩት ይህ አፈጻጸም እስከዛሬ ድረስ በሁሉም የሀምሌ ወራት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ሪከርድን የሰበረ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ሀምሌ ወር ለውጪ ገበያ ከቀረበዉ 40 ሺህ 532 ቶን ቡና ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
በዚህም እስከዛሬ ድረስ በአንድ ወር ውስጥ ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከተገኘው ገቢ አኳያ ሲነጻጸር ሪከርድን መስበር ችሏል፡፡ከእቅድ አንፃር አፈፃፀሙ በመጠን 132 በመቶኛ በገቢ ደግሞ 110 በመቶኛ ብልጫ አለዉ ተብሏል፡፡
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ17 ሺህ 758 ቶን እንዲሁም በገቢ ደረጃ ደግሞ የ54 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ የታየበት ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ በዘንድሮው በጀት አመት ከአንድ ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በ2016 በጀት አመት ከቡና ሽያጭ በመጠንም ሆነ በገቢ ከፍተኛ የሆነ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት 298 ሺህ 500 ቶን ቡና ለውጪ ገበያ አቅርባ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።
ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠንም ሆነ በገቢ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።
የተላከው የቡና መጠን በ20 በመቶ እንዲሁም በዋጋ ደረጃም በ7 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 240 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት ልካ አንድ ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ባለስልጣኑ በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡