በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በቤሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታውቋል።
እስራኤል የሃመስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ እና የሊባሱ ሄዝቦላህ የጦር መሪ ፉአድ ችኩር መግደሏን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።
የኢራንን ዛቻ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት በመንገሱ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረጉ በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን ሀገራትም ዜጎቻቸውን በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።
በቤሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ የቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በሊባኖስ እና በቀጠናው ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ስጋት እና ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን አስታውቋል።
ጽህፈት ቤቱ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ማንኛውንም የተለየ ሁኔታ ሲገጥማቸው በቆንስላው የቀጥታ መስመር ስልክና ዋትሳአፕ እንዲያሳውቁ ጥሪ አስተላፏል።
እንዲሁም ከሊባኖስ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ መመሪያዎችን ወይም ምክሮችን ማክበር ይገባል ያለው ጽህፈት ቤቱ፤ በማንኛውም ሰልፎች ወይም ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ከማድረግ እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
በሊባኖስ እና አካባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከታማኝ የዜና ምንጮች እና አፊሴላዊ ቻናሎች የሚወጡ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ክንውኖችን እንዲከታሉም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
በሊባኖስና በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የፀጥታ ስጋት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርና ሊባስኖስን ለቀው እንዲወጡማዘዛቸው ይታወሳል።
በቤሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፤ የአሜሪካ ዜጎች በተገኘው በማንኛውም የበረራ ቲኬት በአስቸኳይ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰበ ሲሆን፤ ለቀው ለማይወጡ ደግሞ ለረጅም ጊዜ እቅድ እንዲያዘጋጁ እና መጠለያ ምሽግ ቦታ እንዲሆኑ አሳስቧል።
ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የንግድ በረራዎች ከመቋረጣቸው በፊት ሊባኖስን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ማሳሰባቸውም ይታወሳል።
ከሰሞኑ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የጦርነት ስጋት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ግዙፍ የዓለማችን አየር መንገዶች ወደ እስራኤል፣ ሊባኖስ እና ኢራን የሚያደርጉትን በረራ አቁመዋል።
በረራዎች በመሰረዛቸው ምክንያት ከ160 ሺህ በላይ እስራኤላዊያን በበርካታ የዓለማችን ሀገራት ኤርፖርቶች እየተጉላሉ እንዳሉ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢራን እና ሂዝቦላህ ዛሬ ወይም ነገ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ለቡድን ሰባት ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እስራኤል በበኩሏ ከኢራንም ሆነ ሂዝቦላህ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከት ዝግጁ መሆኗን የገለጸች ሲሆን ሳውዲ አረቢያ እና ጆርዳን እስራኤልን ለማጥቃት በሚል ወደ አየር ክልላቸው የሚገቡ ሚሳኤሎችን መተው እንደሚጥሉ ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ ግብጽ ከኢራን እና ሂዝቦላህ የሚተኮሱ ሚሳኤሎችን መትታ እንድትጥል ከእስራኤል የቀረበላትን ተመሳሳይ ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች ተብሏል፡፡