የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ከመስከረም ወር ጀምሮ አየር መንገዳችን ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን ሁሉንም በረራ ማገዱን አሳውቆናል” ብሏል፡፡
ኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀጣዩ መስከረም በኋላ ወደ አሥመራ እንዳይበር ማገዱን የሚያሳውቅ ማስታወቂያ በዛሬው እለት አውጥቷል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን አስመለክቱ በሰጠው መግለጫ፤ “የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ሐምሌ 14 2016 ዓ.ም ወይም በፈረንጆቹ 21 ጁላይ 2024 በላከው ደብዳቤ በፈረንጆቹ ከመስከረም 30 ቀን 2024 ዓ.ም. ጀምሮ አየር መንገዳችን ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን ሁሉንም በረራ ማገዱን አሳውቆናል” ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳዩን አስመልክቶ የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንን ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ጉዳዩም በበጎ መልኩ እልባት እንደሚያገኝ ያለውን ዕምነት ገልጿል።
የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በዛሬው እለት ሓዳስ ኤርትራ” ጋዜጣ ላይ ባወጣው ማስታወቂያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ከመስከረም 20 2017 ዓ.ም ጀምሮ መታገዳቸውን አስታውቋል።
የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በምክንያትነት ከጠቀሳቸው ውስጥም “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ማንገላታት እንዲሁም ካሳ ኣለመክፈል የሚሉ ምክንያቶችን አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ባወጣው መግለጫው በበኩሉ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የላከለት ደብዳ ላይ “ለክልከላ ውሳኔ ያደረሱ ምክንቶችን አልጠቀሰም” ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ ዳግም የጀመረው ከሁለት አስርት ኣመታት በኋላ በ2011 ዓ.ም ላይ እንደበረ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጦርነት ምክንያት ከ20 ዓመታት በላይ ምንም አይነት የትራንስፖርት ግንኙነት ያልነበራቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በ2011 ዓ.ም የአየር ትራንስፖርት መጀመራቸው ይታወሳል።
በወቅቱ የመጀመሪያውን በረራው ወደ አስመራ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ዘመናዊ አውሮፕላን 250 ገደማ ሰዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ መጓዙም አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ከ20 ዓመት በኋላ መሻሻል ቢያሳይም ግንኙነቱ እየተሻሻለ መሄድ አልቻለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስም ሳይጠቅሱ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን የሚሰሩ የጎረቤት ሀገራት አሉ ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳትፎ ያደረገችው ኤርትራ ከደቡብ አፍሪካ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ተጠይቃለች፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር አሁንም የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ አለመውጣቱን፣ በርካታ ቀበሌዎች አሁንም በኤርትራ ጦር እንደተያዙ ከሶስት ወራት በፊት ተናግረው ነበር፡፡
የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በበኩሉ የሀገሪቱ ጦር በግዛቱ ላይ መሆኑን ከኢትዮጵያም የያዙት መሬት እንደሌለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡