በኢትዮጵያ ፓስፖርት ቤት ለቤት ማደል ሊጀመር ነው ተባለ

በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ፓስፖርት ተሰጥቷል ተብሏል

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዓመታዊ አፈጻጸሙን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት በ2016 አመት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ፓስፖርት ለአመልካቾ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በታሪኩ ይህን መጠን ያለዉ ፓስፖርት ለአገልግሎት ፈላጊዎች ሲሰጥ የመጀመሪያዉ መሆኑን ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።

ይህ በዚህ እንዳለም ተቋሙ ከፓስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ክፍያዎች 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንም ተናግረዋል።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ጭምር ቅሬታ ሲቀርብበት ቢሰማም እንዲሁም ተገልጋዮች አሁንም ቅሬታ ማቅረባቸዉን ቢቀጥሉም ፤ ተቋሙ አሰራሮቼን እያስተካከልኩ እገኛለሁ ብሏል።

ዋና ዳይሬክተሯ ፤ ከዚህ ቀደም በየእለቱ የሚታተመዉ ፓስፖርት መጠን 2 ሺህ ብቻ ነበር በተደረጉ ማሻሻያዎች ምክንያት ወደ 14 ሺህ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ አዲስ ፓስፖርት ጠያቂዎች በሁለት ወር ዉስጥ ፓስፖርታቸዉን ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በቀጣዩ አመት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የኢ – ፓስፖርት (E-Passport) አሰራር እንደሚጀምር ይህም የሀሰተኛ ፓስፖርቶችን እና ሰነዶን እንደሚያስቀር ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከነሃሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የፓስፖርት ክፍያ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከቀጣዩ መስከረም ወር ጀምሮ ቤት ለቤት የፓስፖርት እደላ እንደሚጀምርም ገልጿል፡፡

ይህ የቤት ለቤት አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ሳሆን ባለሃብቶች እና ታዋቂ ሰዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት ነው የተባለ ሲሆን ለዚህም የተለየ ክፍያ ይተመንለታል ተብሏል፡፡

እንዲሁም ባለፉት 30 አመታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ መግባትም ሆነ መዉጣት እንዳይችሉ እገዳ ተላልፎባቸው በነበሩ 10 ሺህ ሰዎች ለይ እግድ ማነሳቱ ተገልጿል፡፡

ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡም ሆነ እንዳይወጡ ታግደዉ የነበሩ 10 ሺህ ሰዎች እግድ እንደተነሳላቸዉ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተናግረዋል።

አገልግሎቱ እግዱን ያነሳዉ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጸድቆ በተሰጠዉ ስልጣን እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።

በቅርቡ የጸደቀው አዋጅ የሀገር ጥቅምን ይነካሉ ተብሎ የተለዩ ሰዎች ወደ ሀገር ለመግባትም ሆነ ለመዉጣት ሲፈልጉ እግድ የሚጥለዉ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሆኑን ደንግጓል።

ይህ አዋጅ በተለይም በህግ አዋቂዎች ትችት ሲደርስበት የቆየ ሲሆን ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሰላማዊት ማብራሪያ ሰጥተዉበታል።

ዋና ዳይሬክተሯ ከዚህ ቀደምም የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እግድ ይጥል ነበር ያሉ ሲሆን አዲሱ አዋጅ ይህን አሰራር ወደ ዋና ዳይሬክተሩ የሚለዉጥ መሆኑን ገልጸዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *