የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት 93 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
ከተገኘው ገቢ 39.9 በመቶ የድምጽ ፣ 21.7 የኢንተርኔት ፣10.2 የዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ፣ 2.5 ከቴሌብር እና 1.5 ከኢንፍራስትራክቸር እንዲሁም 5 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከዲቫይስ የተገኘ ገቢ መሆነም ተገልጿል ።
በበጀት ዓመቱ የኩባንያው የደንበኞች ቁጥር 78 ነጥብ 3 ሚሊየን መድረሱን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ 21 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንም ተናግረዋል።
ኩባንያው በውጭ ምንዛሬ ገቢ ከሚያገኝባቸው ምንጮች 198 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አክለውም በ2016 በጀት ዓመት ኢትዮ ቴሌኮም 30 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ግብር መክፈሉንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም 374 የፊክስድ ብሮንድ ባንድ አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም 570 ኪ.ሜ የፋይበር ጥገና በማድረግ እና 16 ተዘግተው የነበሩ ጣቢያዎችን ወደ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
በመግለጫቸውም ኩባንያው በዓለም ካሉ 778 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች 17ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም በአፍሪካ ካሉ 195 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ መቻሉን ገልጸዋል።
በቴሌብር አገልግሎት የደንበኞቹን ቁጥር 47 ነጥብ 55 ሚሊየን ማድረሱን የገለጹት ሃላፊዋ የቴሌ ብር ግብይት መጠን ከ2 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ትሪሊየኑ በ2016 በጀት ዓመት የተዘዋወረ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው በጀት ዓመት ከአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎቶች 90 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ የነበረ ሲሆን 94 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ የኑሮ ውድነት፣ የጸጥታ እና ደህንነት ችግሮች እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተቋሙ ስራዎች ላይ ስጋት መሆናቸው ተገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም ካሉት 78 ሚሊዮን ደንበኞች ውስጥ 42 በመቶዎቹ ዘመናዊ ስልክ እንዳላቸው ስራ አስፈጻሚዋ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡