ኢትዮጵያዊያኑ በሞሮኮ በተካሄደ የቴክኖሎጂ ውድድርን በአንደኝነት አጠናቀቁ

የኢትዮጵያ ቡድን በሞሮኮ በተካሄደው የሁዋዌ ቴክ ፎር ጉድ ክፍለ አህጉራዊ ውድድርን በአንደኝነት አጠናቋል፡፡

የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር “Huawie Seeds for the Future 2024” የቴክኖሎጂ ስልጠና መርሃ ግብር በሞሮኮ (ኢሳዉራ) ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል።

ይህ ስልጠና ከምስራቅ፣ ሰሜን፣ ምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ የተውጣጡ 17 አገራትን አሳትፏል። ኢትዮጵያም ከስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 10 ተማሪዎችን በስልጠናው ያሳተፈች ሲሆን ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 5 ተማሪዎችን የያዘው የኢትዮጵያ አንድ ቡድን በሁዋዌ ቴክፎርጉድ ክፍለ አህጉራዊ ውድድር አንደኛ በመሆን አሸንፏል፡፡

ተማሪዎቹ በቴክ ፎር ጉድ ክፍለ አህጉራዊ (ግሎባል) ፕሮጀክት ከመወዳደራቸው በፊት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስልጠናዎችን ወስደዋል።

ተሳታፊ ተማሪዎቹ በ28 ቡድኖች ተከፋፍለው ለውድድር የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ያዘጋጁ ሲሆን አምስት ተማሪዎችን ያቀፈው አንደኛው የኢትዮጵያ ቡድን  የሞሮኮ ቡድንን  አስከትሎ አንደኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቋል። በዚህም  ያሸነፉት ሁለቱ ቡድኖች (ኢትዮጵያና ሞሮኮ) በ2025 ለሚካሄድው አለም አቀፍ ፍፃሜ ወደ ቻይና ያቀናሉ።

የፕሮጀክቱ ስም “EarlyVet” ሲሆን የእንስሳት በሽታዎችን አስቀድሞ ለማወቅ የሚረዳ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)ን በሚጠቀም ቴክኖሎጂ ላይ ያተኩራል።

ተማሪዎቹ እንደገለጹት ፈጠራቸው ሁለተኛውን እና አስራ አምስተኛውን የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኮረ ነው።

ሚስተር ሊሚንግ ዬ የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተማሪዎቹ ባስመዘገቡት ውጤት መደሰታቸውን ገልጸው የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ፕሮግራም ተልዕኮ ወጣቶች በፍጥነት የሚለዋወጥን አለም ለመጋፈጥ የሚያስችሉ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን እና አስተሳሰቦችን እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብለዋል።

እ.ኤ.አ. በ2008 በሁዋዌ የተጀመረው መርሃ ግብሩ ወጣት ተሰጥኦዎችን ለማዳበር ፣የእውቀት ሽግግርን ለማሳደግ ፣በአይሲቲ ኢንደስትሪ ላይ የበለጠ ግንዛቤን እና ፍላጎትን ለማስተዋወቅ እና በዲጂታል ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ ተሳትፎን ለማበረታታት ያለመ ነው። ሁዋዌ በኢትዮጵያ ይህንን ፕሮግራም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይሰራል።

የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ስልጠና የክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን፣ ፣ ሳይበር ደህንነትን፣ 5ጂን፣ አይኦቲ እና ቢግ ዳታንን ይሸፍናል። እንዲሁም ለባህላዊ ልውውጥ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ክህሎቶችን ለመማር እድል ይፈጥራል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *