ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ከመነጋገር ይልቅ ወደ ሌሎች ሀገራት ሽምግልና ይልካሉ ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የገቡበትን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በንግግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ አይደለችም ሲሉ ተናገሩ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በአገሪቱ ምክር ቤት የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ መንግሥታቸው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን ለማርገብ ፍላጎት ቢኖረውም፤ ኢትዮጵያ ግን ለውይይት ዝግጁ አይደለችም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጥቂት ቀናት በፊት “የሶማሊያ መንግሥት እኛን ከማናገር፣ በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል” ብለው ከተናገሩ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ላይ ስለ ሶማሊያ ጉዳይ ሲናገሩ፤ “እኛን ለመክሰስ አገር ለአገር መሄድ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባ በቀጥታ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን. . . ” ብለው ነበር።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የገቡበትን ቀውስ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ጨርሶ ሊያነጋግረን አልሞከረም ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒትር አብይ አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት አገር ወቅታዊ ጉዳዮችን በትብብር ለመፍታት አናግራን አታውቅም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በአንጻሩ “እየተዘዋወሩ ሽምግልና ይጠይቃሉ” ሲሉ በተመሳሳይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት የታወከ ሲሆን ሞቃዲሾ የኢትዮጵያን አምባሳደር ለቆ እንዲወጣ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በሶማሊያ ለተወሰዱ እርምጃዎች ዝምታን የመረጠች ሲሆን ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት የየትኛውንም ሀገር ሉዓላዊነት እንዳልጣሰ ገልጻለች።
ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በወደብ ጉዳይ የገቡበትን ግጭት ለማስማማት ማደራደር የጀመረች ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአንካራ ተገናኝተው ተመካክረዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የአናካራ ድርድር ከሁለት ወር በኋላ በድጋሚ በአንካራ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን ይህ ድርድር ከውጭ ጣልቃ ገብነት ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መንገድ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ለይ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እያደረጉት ባለው ድርድር የወደብ ጉዳይ ብቸኛው አጀንዳ አለመሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በተሰማራው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወይም አትሚስ ቀጣይ ጦር አሰፋፈር ሁኔታ እና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ እየተደራደሩ መሆኑንም አንስተዋል።