ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ድርድር ጀመሩ

ቱርክ ግንኙነታቸው የሻከረውን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ማደራደር መጀመሯ ተገልጿል።

ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ድርድሩ በቱርክ መዲና አንካራ በመካሄድ ለይ ይገኛል።

ይሁን እንጂ አደራዳሪዋ ቱርክም ሆነች ተደራዳሪዎቹ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።

የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሙአሊም ፊቂ የመሩት ልኡክ በትናንትናው እለት ወደ ቱርክ ማቅናቱን ቢዘግቡም የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጫ አልሰጠም።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣንም በአንካራ ተጀምሯል ስለተባለው ድርድር ምንም መናገር አንፈልግም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የሶማሊላንድ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው በድርድሩ ላይ እየተሳተፉ እንዳልሆነ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጥር ወር ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው የወደብ ስምምነት ምክንያት የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ግንኙነት መሻከሩ ይታወቃል።

ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ናት የምትለው ሶማሊያ በጥር ወር የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት “ህገወጥ እና ሉአላዊነቴን የተዳፈረ ነው” በሚል የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች።

በሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች እንዲዘጉ ወስና የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሪቱ እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ካልሰረዘች በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎችን አስወጣለሁ ማለቷም አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለወራት የዘለቀውን ውጥረታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥረት መጀመሯ የተነገረላት ቱርክ የሶማሊያ መንግስት አጋር ናት።

ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በፈረንጆቹ 2011 በሞቃዲሾ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ አንካራ የሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎችን ማሰልጠን የጀመረች ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችንም ስትገነባ ቆይታለች።

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ስምምነት ከደረሱ ከአንድ ወር በኋላም ቱርክና ሶማሊያ የ10 አመት የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

ስምምነቱ ቱርክ የሶማሊያን የባህር ሃይል ለማጠናከርና የሽብር ስጋትን በጋራ ለመመከት የሚያስችል ነው ተብሎ ነበር።

የሶማሊያን የባህር ክልል ለመጠበቅ ትውላለች የተባለች የቱርክ መርከብም በቅርቡ ሶማሊያ መድረሷ ይታወሳል።

ከኢትዮጵያም ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ቱርክ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የገቡበትን ግጭት በድርድር ለማስታረቅ ሸምጋይ ሆናለች ተብሏል።

የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ከአንድ ወር በፊት በሰጡት መግለጫ የመጀመሪያውን የሀገርነት እውቅና ከኢትዮጵያ እንደሚያገኙ በምትኩም ኢትዮጵያ የባህር በር በሶማሊላድ ታገኛለች ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በአዲስ አበባ ስለተፈረመው የሶማሊላንድ ወደብ ስምምነት ዙሪያ የአቋም ለውጥ እንደሌለ በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *