ኢትዮጵያ የዳሌና ጉልበት መገጣጠሚያ ንቅለ ተከላ ሕክምና መስጠት ጀመረች

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሙሉ ዳሌና ጉልበት መገጣጠሚያ ቅየራ ህክምና በየካቲት 12 ሆስፒታል መሰጠት ተጀመረ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአጥንት ቀዶ ህክምና እና የመገጣጠሚያ ቅየራ ከፍተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎትን በይፋ መሰጠት መጀመሩን አስታውቋል።

የአጥንት ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት እና የመገጣጠሚያ ቅየራ እንዲሁም የአርትሮስኮፒ  ህክምና ሠብ ስፔሻሊስት ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ መሐመድ እንደተናገሩት  በአሁኑ ወቅት የሙሉ ዳሌ እና ጉልበት መገጣጠሚያዎች ቅየራ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎትን ሆስፒታሉ በይፋ መስጠት ተጀምሯል።

በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳን የዳሌ መገጣጠሚያ ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ በሌላ  ሰው ሰራሽ በሆነ አካል በመተካት ይህ አይነቱ ህክምና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ይህ አገልግሎት በኢትዮጵያ ህክምና ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሠጥ ሲሆን በዳሌና ጉልበት የመገጣጠሚያ ህመም የተነሳ ለመራመድ እና ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩ በርካታ የችግሩ ሰለባ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

እንዲህ ያለው ህክምና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ሳያገኙ የሚቀሩበትና ለከፋ የህመም ስቃይ የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩን  የህክምና ባለሙያው ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ ይህንን አገልግሎት ለበርካታ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ሲሉ ዶክተር ሰኢድ ተናግረዋል ።

ለዳሌ መገጣጠሚያ ህመም መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የገለፁት የህክምና ባለሙያው በአግባቡ ያልታከመ የመገጣጠሚያ ኢንፌክሽን ፣ የቁርጥማት ህመምና ከዚህ ቀደም ሳይታከሙ የቀሩ ሌሎች የመገጣጠሚያ ህመሞች ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ወደ መገጣጠሚያ ጭንቅላት የሚደርስ የደም ዝውውር መቀነስን ጨምሮ የአልኮል መጠጥን አዘውትሮ መጠቀም አባባሽ መንስኤዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ማንኛውም ሰው እንዲህ ያሉ የዳሌ መገጣጠሚያ ህመም ምልክቶችን በሚመለከትበት ወቅት በቶሎ ወደ ህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ቀርቦ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ቢችል ለከፋ ህመም እንዳይጋለጥ ይረዳዋል ሲሉ የህክምና ባለሙያው ምክራቸውን ለግሰዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *