ኢሕአፓ ያስቀመጣቸው ቅድመሁኔታዎች እስከሚሟሉ ድረስ ከዛሬ ከግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ እራሱን ከሀገራዊ ምክክሩ ያገለለ መሆኑን አስታወቋል።
ኢሕአፓ ኮሚሽኑ ሲመሠረት ከነበረው እውነታ ባሻገር የተፈጠሩ ግጭቶችን ለሀገራችን ቀውስም ወሳኝ ቦታ ያላቸው ሁኔታዎችን ለማካታት የሚያስችል ተልዕኮም ይሁን ህጋዊ ማዕቀፍ አለመኖሩ አሁን እየተካሄደ ባለበት መልኩ የኮሚሽኑ የሥራ ውጤት በአገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ያመጣል ብሎ እንደማያምን ገልጿል።
ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፉ የመጡትን ቀውሶች በአገራዊ በቅንነት ምናልባት በድርድርና ምክክር ሊፈቱ ይችሉ ይሆናል በሚል ተስፋ ለተወሰኑ ዐመቶች ሲሳተፍባቸው የቆየ መሆኑን በመግለጽ ”ገዥዎቻችን ችግሮችን በቅንነትና በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ አገራዊ ምክክርና መግባባትን የራሳቸውን ሥልጣን ማጠናከሪያና የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ማደናገሪያ” አድርገው ሲጠቀሙበት ቆይተዋል ብሏል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የምክክር ኮሚሽን ከትላንትና ከትላንት ወዲያው ስህተት ትምህርት ባልወሰደ ሁኔታ ሲዋቀር ገና ከጅምሩ በጥርጣሬ እንዲታይ ሆኗልም ብሏል።
የኮሚሽኑ የአመሠራረት ሂደት የተቃዋሚውን ግብዓት በተግባር ያካተተ አለመሆኑ፣ ለብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አባልነት ተጠቆሙ የተባሉት 620 ተወዳዳሪዎች እነማን እንደነበሩ ከመጀመሪያው በግልጽና በይፋ አለመታወቁ፣ ከ620ዎቹ መካከል ለሕዝብ ይፋ የተደረጉት 47 ዕጩዎች ውስጥ የውጭ ዜግነት ያላቸው፣ የኢህአዴግ አባላት የነበሩ ዲፕሎማቶች፣ የክልል መሪዎች…ወዘተ መካተታቸውን በመግለጫው ጠቁሟል።
በተጨማሪም ከተሾሙት 11 ኮሚሽነሮች ውስጥ በ43ቱ የስም ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ሦስት ግለስቦች ድንገት መጨመራቸው በተመራጭ ኮሚሽነሮች ገለልተኛነትና በሂደቱ ተዓማኒነት ላይ ጥላ ያጠላበት በመሆኑ፣ የኮሚሽኑን አካሄድ በተመለከተ ሂደቱ ከታች ወደላይ መሆኑ ጥሩ ሆኖ ሳለ የተሳታፊዎች አመላመል ግን የገዥውን ፓርቲ የበላይነት እንዲኖረው የተመቻቸ መሆኑን ገልጿል።
የመንግሥት የሥራ ቋንቋን፣ የአዲስ አበባ ክልላዊ አስተዳደርን ጉዳይ፣ አዳዲስ ክልሎች የመፍጠር ጉዳይ፣ የሽግግር ፍትኅ ጉዳይ….ወዘተ እንዲሁም ራያ፣ ወልቃይትና ጠገዴን በተመለከተ ገዥው ፓርቲ በኮሚሽኑ አማካይነት ወደ መግባባት ሊደረስባቸው ይችላል የሚባሉትን ጉዳዮች ቀድሞ እየወሰነባቸው መታየቱ በኮሚሽኑ ሥራ ውስጥ ጣልቃ እየገባ መሆኑን እንደሚያሳዩ አንስቷል።
የኮሚሽኑ ተጠሪነት በብልጽግና ቁጥጥር ሥር ለሚገኘው ፓርላማ በመሆኑ ኮሚሽኑ የተቻለውን ያህል ጥረት ቢያደርግም በመጨረሻ ገዥው ብልጽግና ከሚፈልገው ውጭ ተግባራዊ የሚሆን ነገር አይኖርም የሚለውን ከፍተኛ ስጋት መደቀኑ የኮሚሽኑን ውጤታማነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ አንዲገባ አድርጎታልም ብሏል።
ሀገራዊ ምክክርና መግባባት የሀገሪቱን የቆዩም ሆኑ የአሁናዊ ችግሮች ለመፍታት የሀገሪቱን አሁናዊ ሁኔታ ኮሚሽኑ ሲመሠረት ከነበረው ሁኔታ ጋር እጅግ እንደሚለያይ አንስቷል።
ኢሕአፓ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከምሥረታው ጀምሮ ችግር የነበረበት በመሆኑ፣ የኮሚሽኑን የሥራ ውጤትም የሚቀርበው ለገለልተኛ አካል ሳይሆን በብልጽግና አባላት ለተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ከብልጽግና ፓርቲ ጥቅም አኳያ በመመርመር የኮሚሽኑን የሥራ ውጤት ሊቀበለውም ሆነ ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችል እንደሚያምን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በተሻለ መልክ ተዋቅሮ ገለልተኛነቱም አስተማማኝ እስካልሆነ ድረስ፣ ምንም እንኳን የኮሚሽኑ አባላት በቅንነት ሥራቸውን ሊያከናውኑ ይችላሉ የሚል ዕምነት ቢኖረንም፣ አሁን ባለው አወቃቀር አካሄድ፣ የፖለቲካ አውድ፣ የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ድምዳሜ ላይ ሊደረስ ይችላል የሚል ዕምነት እንደሌለው አስታውቋል።
በተጨማሪ ኮሚሽኑ ሲመሠረት ከነበረው እውነታ ባሻገር የተፈጠሩ ግጭቶችን ለሀገሪቱም ቀውስም ወሳኝ ቦታ ያላቸው ሁኔታዎችን ለማካታት የሚያስችል ተልዕኮም ይሁን ህጋዊ ማዕቀፍ አለመኖሩ አሁን እየተካሄደ ባለበት መልኩ የኮሚሽኑ የሥራ ውጤት በአገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ያመጣል ብሎ ኢሕአፓ እንደማያምን ገልጿል።
ኢሕአፓ ከዚህ ሂደት ውስጥ ከዛሬ ከግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ ከላይ በቅደመ ሁኔታ ያስቀመጥናቸው እስከሚሟሉ ድረስ እራሱን ያገለለ መሆኑን አስታውቋል።
በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ፣ የሲቪክ ድርጅቶችና ሌሎች ባለደርሻዎችም ለዚህ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ ኢሕአፓ ጥሪውን አቅርቧል።
ብልጽግናም የድርጅቱን ጥሪ በቅን መንፈስ ተመልክቶ ለአስቸኳይና ለሁሉን አቀፍ ድርድር ራሱን አንዲያዘጋጅ፣ ሀገራችን ከአውዳሚ ጦርነቶች ወጥታ ህዝቡም የሠላም ዐየር የሚተነፍስበት ሁኔታ እንዲፈጠርና እንዲሁም በምንም መልኩም ለሠላማዊ ፖሊቲካዊ መፍትሄዎች ፍለጋ የሚደረጉ ጥረቶችን ብልጽግና እንዳያደናቅፍ ሲል ኢሕአፓ ጥሪውን አስተላልፏል።