የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ በመንግስት ጫና እየተደረገበት እንደሆነ ገለጸ

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ የሚደረገው ወከባ እና እስር እንዲቆም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጠይቋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መንግስት ከፍተኛ ጥቃትና ጫና እየፈጸመበት እንደሆነ ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

ኢሰመጎ በመግለጫው በመንግስት እየደረሰበት ያለው ጥቃት እና ጫና አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለጫው ላይ አሳውቋል።

ጉባኤው በተለያዩ ጊዜ ተፈጽመውብኛል ያላቸው ጥቃቶች እና ከፍተኛ ጫናዎች በመግለጫው ላይ የዘረዘረ ሲሆን በተቋሙ አመራር ላይ በመንግስት የደህንነት ሰዎች የሚፈጸም ክትትል ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየጨመረ መምጣታቸውን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ክትትል ስራችሁን ካላቆማችሁ ፤ መንግሥትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት መወንጀል ካላቆማችሁ  ‘ ዋጋ ትከፍላላችሁ ‘ የሚል ዛቻ እየደረሰበት መሆኑን ገልጿል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ስራ በሚሰሩ ሰራተኞች ላይ የመንግስት ጸጥታ አካላት አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ መሳደብ፣ ማንገላታት፣ ስራቸውን እንዲያቆሙ እያስፈራሯቸው እንደሆነም ድርጅቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

ተቋሙ አክሎም ምንም እንኳን ኢሰመጉ ላለፉት 32 ዓመታት በሀገሪቱ ህግ አግባብ ተመዝግቦ እየሰራ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ሰዎች ” ፍቃድ የላችሁም ” በማለት ማስፈራራትና የእስር ዛቻ እየተሰነዘረባቸው እንደሆነም አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የድርጅቱ አባላት ላይ ከህግ ውጭ እስር መፈጸም እና ወደ ፍርድ ቤት አለማቅረብን ጨምሮ በተለይም በአዲስ አበባ ተገቢ ያልሆኑ ክሶችን ለመመስረት እንቅስቃሴ ማድረግ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩብኝ ነውም ብሏል፡፡

የኢሰመጉ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ከሀገር ውጭ ካሉ ስራዎችና ስብሰባዎች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ማንገላታት ፣ ማዋከብ ፣ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር ” 13/2011 ” መሠረት ሐገር በቀል ድርጅት ሆኖ በ1984 ዓ.ም የተመሠረተ መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በበኩሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እስርን አውግዟል፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ሀይለመስቀል እንዳሉት የኪነ ጥበብ ስራዎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጫ መንገድ በመሆኑ ከጥቃት ሊጠበቅ እና ባለሙያዎችም ለእስር ሊዳረጉ አይገባም ብለዋል፡፡

መንግስት ለኪነ ጥበብ ሙያ እና ባለሙያዎች ልዩ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ያሉት አቶ ያሬድ ኪነ-ጥበብ ለሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ መዳበር፣ መጎልበት እንዲሁም  መስፋፋት እና መከበር ያለው ጉልህ ሚና እጅግ የላቀ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የኪነ-ጥበብ መድረኮች እና ባለሞያዎች በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በግጥም፣ በስዕል እና በቅርፃቅርፅ መልክ የሚያንጸባርቋቸው ሃሳቦች የዜጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መገለጫዎች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እነዚህ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ለአንድ ማህበረሰብ የደስታም ሆነ የብሶት ሃሳቦቹን የሚገልጽባቸው መንገዶች የመሆናቸውን ያህል በአገር አስተዳደር ኃላፊነት ላይ ለተቀመጡ ወይም ለመንግስት አካላት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄዎች፣ ስጋቶች፣ እርካታዎች ወይም ብሶቶችን በማድረስም ረገድ ልክ እንደ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው።  

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወድህ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና የጥበብ ሥራዎች ወይም የኪነ-ጥበብ መድረኮች ላይ እየደረሱ ያሉ ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እስሮችና ጫናዎች ከዕለት ዕለት እየበረቱ መምጣታቸው ድርጅታችንን ያሳስበዋል ብሏል፡፡

ከነዚህም ውስጥ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ወቅታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበረዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት ተከታታይ “ቧለቲካ” የቴአትር መድረክን፣በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም ማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት “እብደት በህብረት” የተሰኘው የመድረክ ተውኔት አዘጋጅና ተዋናይ ባለሙያዎች መታሰራቸውን ድርጅቱ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም የተለያዩ እንደ ስነ-ፅሁፍ፣ ተውኔት እና የመሳሰሉት ስራዎች የሚቀርቡባቸው የጥበብ መድረኮች የስብሰባ ፍቃድ ያስፈልጋችኋል በሚል እየተስተጓጎሉ ነውም ብሏል፡፡

መንግስት በህገ-መንግስቱ እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ የተደረገለትን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንድያከብር እና በዘፈቀደ እንዳይጣስም ጥበቃ እንድያደርግ፤ መንግስት ጥበብ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና እና ፖለቲካዊ እድገት ያለውን ፋይዳ  ከግንዛቤ በማስገባት ለጥበብ ባለሙያዎች እና ስራዎቻቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ምህዳሩን  በማስፋት ሀላፊነቱን እንዲወጣም ማዕከሉ ጠይቋል፡፡

እንዲሁም በሥራቸው ምክንያት የታሰሩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከእስር እንዲፈቱ ወይም የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙና የተከለከሉ የኪነ-ጥበብ መድረኮችም በነጻነት እንዲሰሩ ጥሪውንም አቅርቧል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *