ትምህርት ሚኒስቴር ከገንዘብ ብክነት ጋር በተያያዘ የሶስት ዩንቨርሲቲዎችን ፕሬዝዳንት ከሀላፊነት አንስቷል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት እንደተገለፀው ዩንቨርሲቲዎች የበጀት ብክነት ፈጽመዋል ተብሏል።
የወላይታ ሶዶ፣ የጋምቤላ እና ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲፕሬዝዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ትምህርት ሚኒስቴር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረገው የስራ ግምገማ ወቅት አስታውቋል፡፡
ለአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ እና ሌሎች አራት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሠራው የተቋማት ኦዲት ሪፖርት የ2014 በጀት ዓመት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ከተሰጣቸው 24 መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 13 ተቋማት ላይ አስተደደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡
ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ለደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ለጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና ለቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሠጠቱንም ሚኒስትሩ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ከሁለት ወራት በፊት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረጉት የበጀት ኦዲት ግምገማ ላይ 18 የሶስተኛ ድግሪ ትምህርት የተላኩ መምህራን ደብዛቸው እንደጠፋ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የዩንቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወደ ውጭ ሀገራት እና ሀገር ውስጥ ዩንቨርሲቲዎች የተላኩ 18 መምህራን ትምህርታቸውን በተቀመጠላቸው ጊዜ አጠናቀው እንዳልተመለሱ እና የመመለሻ ጊዜያቸውም እንዳለፈ በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡
በዩንቨርሲቲው ህግ መሰረት አንድ የዶክትሬት ወይም የሶስተኛ ድግሪ ትምህርትን ለማጠናቀቅ አራት ዓመት በቂ ሲሆን በተለያዩ አስቸጋሪ ምክንያቶች ትምህርቱን ማጠናቀቅ ላልቻሉ ደግሞ ሁለት ዓመት እንዲጨመርላቸው ይፈቅዳል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡
ይሁንና እነዚህ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ከተላኩ መምህራን መካከል ትምህርታቸውን በስድስት ዓመታት ውስጥ አጠናቀው ባለመምጣታቸው ከስራ መባረራቸው ተገልጿል፡፡
እነዚህ የቀድሞ የዩንቨርሲቲው መምህራን ከስራ በመባረራቸው ምክንያት ለትምህርት ስፖንሰር፣ ደመወዝ እና ትራንስፖርት ወጪ የወሰዱትን ገንዘብ ማስመለስ አለመቻሉን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ከ18ቱ ውስጥ አምስቱ ከሀገር ውጪ መሆናቸውን በማረጋገጣችን ዋሶቻቸው ላይ ክስ መስርተን ውሳኔው ለእኛ ተወስኖልናል ማስመለስ እንጀምራለን ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም 15ቱ ቀሪ የቀድሞ መምህራን ግን በሀገር ውስጥ እንዳሉ እና የትኛውም ተቋም እንዳልተቀጠሩ አረጋግጠናል ነገር ግን ከደመወዛቸው እና ስራቸው ስላገድናቸው ገንዘቡን ተመላሽ ማድረግ አልቻልንም ሲሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡