በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ከግንቦት 5 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ 40 ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል፡፡
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ንጹሃኑን የገደሉት ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ የነበሩ እና የሰርግ ስነስርዓትን ታድመው ሲመለሱ እንደሆነ አሻም ቲቪ ዘግቧል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች እንዳሉት በአካባቢው ከዚህ ቀደም ብሎ ግንቦት 4 በፋኖ ሀይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ውጊያ እንደነበር ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም በስጋት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ባህርዳር እና ወደ ሌሎች ገጠራማ አካባቢዎች መሰደዳቸውን ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ እድሜአለም አንተነህ በበኩላቸው በአካባቢው ውጊያ እንደነበር ገልፀው ነገርግን አንድም ንፁሃን አልተገደለም ማለታቸውን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ስር ባሉት ሁለት ወረዳዎች በተደረጉ ሁለት የድሮን ጥቃቶች መምህራንን ጨምሮ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት ቀርቶታል።
በአማራ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ምዕራባዊያን ሀገራት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቅሰዋል፡፡