የገንዘብ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት እቅዱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
ሚኒስቴሩ ባቀረበው የፋይናንስ ሪፖርቱ ላይ እንዳለው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከብድር እና እርዳታ 4 ነትብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብሏል፡፡
ከተገኘው ከዚህ ውስጥ 54 በመቶው ዕርዳታ ነው የተባለ ሲሆን 849 ሚሊዮን ዶላር በብድር የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከተገኘው ገቢ ውስጥም የዓለም ባንክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ፈሰስ አድርጓል የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላትም አስታውቃለች፡፡
ከሀገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ 356.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ ታቅዶ 338 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩ የመንግስት ድርጅቶች በዘጠኝ ወር ውስጥ ከወቅታዊ እና ከውዝፍ ዕዳ ብር 760 ሚሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 739 ሚሊዮን መሰብሰቡንም የገንዘብ ሚኒስቴር በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
ከማዕከላዊ ግምጃ ቤት 470 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል ያለው የገንዘብ ሚኒስቴር ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ለ2016 በጀት ዓመት ከተፈቀደዉ 153.5 ቢሊዮን ብር ተከፍሏልም ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ያለባት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹ ከቻይና የተገኘ ሲሆን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላት በመጠየቅ ለይ ትገኛለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ከታማኝ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከፍላለች ብለዋል፡፡
የብድር ጫና ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከቻይና ውጪ ያሉ ሀገራ እና አበዳሪ ተቋማት የብድር መክፈያ ጊዜን እስካሁን ለማራዘም ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡
ኢትዮጵያ እና ዓለም ከሁለት ሳምንት በፊት ባንክ የ1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ97 ቢሊዮን ብር እርዳታ እና ብድር ስምምነት መፈራረማቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ጦርነት፣ ኮሮና ቫይረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኑሮ ውድነት እና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየፈተኑ ያሉ ክስተቶች ሲሆኑ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ቢቆምም ሌላ ጦርነት በአማራ ክልል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ምክንያት በቀይ_ባሕር የሚፈጸሙ ጥቃቶች በ ኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ ንግድ አንቅስቃሴ ላይ ችግር መፍጠራቸውን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ገልጿል፡፡
ተቋሙ እንዳለው በቀይ ባሕር የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ትልልቅ የመርከብ ኩባንያዎች ወደ ጅቡቲ ወደብ ሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማቆማቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እና የሚወጡ ጭነቶች እንዳይገቡና እንዳይወጡ ችግር ሆኗል ብሏል፡፡
አጓጓዥ መርከብ ድርጅቶች በአሁኑ ሰዓት ወደ ጅቡቲ መምጣት ቀንሰዋል ብሎም አቁመዋል ያለው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይ የኢትዮጵያን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑ የወጪ ንግድ እንዲቀንስ ምክንያት እንደሆነም ገልጿል፡፡