የኢትዮጰያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ አሥር ቀናት ውስጥ ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚያመላክቱን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሰፊ ቦታዎችን ያካተተና የተጠናከረ ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተስፋፋ ዝናብ የሚኖር ሲሆን እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጲያ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸውም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና፤ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ፤ ነአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም እና አዊ ዞኖችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ላይ የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል፡፡
በሌላ በኩል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ፣ ስልጤ ፣ በአዲስ አበባ፣ ድሬ ዳዋ እና ሃረር ላይ ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጥል ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ማስጠንቀቂያ በኢትዮጵያ በጎርፍ አደጋ ምክንያት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብሎ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት ሦስት ወቅቶች ውስጥ አንዱ የሆነውና አራት ወራትን የሚይዘው የበልግ ወቅት በደቡብ አጋማሽ ለሚገኙ የአገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው።
ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉትን ወራቶችን በሚሸፍነው የበልግ ወቅት ለሶማሌ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ለደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች 55 በመቶ የዝናብ ስርጭታቸውን በዚህ ወቅት ያገኛሉ።
የበልግ ወቅት ለምስራቅና ደቡብ ትግራይ፣ ለሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ለአማራና ኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ ለመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢ፣ ለምስራቅ አካባቢዎች (ሀረርና ድሬዳዋ) ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ተደርጎ ይወሰዳል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሀገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ብቻ ከ12 በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ ተገለጿል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በደረሱ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋዎች የሠው ሕይወት እልፈትና ለንብረት ጉዳት ደርሷል።
ይህ በዚህ እንዳለ በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት ድርቅ የሚከሰት ሲሆን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለእርዳታ ተዳርገዋል፡፡
በተለይም በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል በሶማሊ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞኖች እንዲሁም በደቡባዊ ኢትዮጵያ በኩል ያለው አካባቢ በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በጦርነት እና ድርቅ ምክንያቶች ለእርዳታ የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ በመምጣት ላይ ይገኛል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን እንዲሁም 21 ህጻናት ደግሞ ህይወታቸው አልፎ መወለዳቸውን አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።