ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ በዋዜማ ሬዲዮ፣ ኢኤምኤስ እና ሌሎችም ሚዲያዎች በጋዜጠኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሸገር ከተማ “ሕገ ወጥ ግንባታ” ናቸው ተብለው በፈረሱ ወደ 100 ሺህ የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችና በተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ለዘገባ ወደ ስፍራው ባመራበት ወቅት በፖሊስ ተይዞ ለእስር ተዳርጎም ነበር፡፡
በዚህ ወቅት በፖሊስ ድብደባ፣ እስርና ማዋከብ ደርሶበት እንደነበር የተናገረው ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ በዋስ ከእስር ቤት ወጥቶ እንዲከራከር በፍርድ ቤት ተወስኖለት ቢወጣም ዛቻና ማስፈራሪ ሲደርስበት እንደነበረ ለኢትዮ ነጋሪ ተናግሯል፡፡
በቅርቡም ለዋዜማ ሬድዮ እና ኢንተር ኒውስ ዘገባ ለመስራት ወደ አማራ ክልል ደሴና ሐይቅ ከተሞች በተጓዘበት ወቅት በክልሉ ኮማንድ ፖስት ታስሮ እንደነበረም አክሏል።
አስቀድሞ በታሰረበት ጉዳይ ለዋስትና የተያዘውን ገንዘብ ለማስለቀቅ ሸገር ከተማ በተገኘ ወቅት ፖሊስ ይዞት እንደነበረ እና በተጨማሪም ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ VOA ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ጉዳይ ፌደራል ፖሊስ ለጥያቄ ትፈጋለህ ብለው አስገድደው ወስደውት እንደነበረ የገለጸው ጋዜጠኛው በደረሰበት ተደጋጋሚ ጫና ምክኒያት አገር ለቆ መውጣቱን ለኢትዮ ነጋሪ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ከተጽእኖ ነጻ ሆኜ የመስራት ፍላጎት ቢኖረኝም የመንግስት ተጽዕኖ ሊያሰራኝ ባለመቻሉ የምወዳት ሀገሬን ጥዬ ለመሰደድ ተገድጃለሁ ሲልም ጋዜጠኛ ሳሙኤል ተናግሯል፡፡
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጋዜጠኞች ለእስር እና እንግልት እየተዳረጉ መምጣታቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው ሪፖርቶች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ከ18 በላይ ሀገራት በኢትዮጵያ የፕረስ ነጻነት መባባሱን ጋዜጠኞችም ለእስር እና እንግልት መዳረጋቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ለይ አስታውቀው ነበር፡፡
መንግስት በበኩሉ በኢትዮጵያ የሚዲያዎች ነጻነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መሻሻሉን ፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉን እና ኢምባሲዎቹ ያወጡት መግለጫ ተቀባይነት የለውም ሲል አስተባብሏል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሲፒጄ እና ሂማን ራይትስ ዋች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለአግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞች መኖራቸውን በመግለጽ ባለስልጣናት እንዲለቋቸው በተለያየ ጊዜ ጠይቀዋል።
የጋዜጠኞቾ መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ ከወራት በፊት ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ስምንት ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ውስጥ ሁለተኛ የጋዜጠኞች አሳሪ ሀገር አድርጓታል።
እንደ ሲፒጄ ሪፖርት ከሆነ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን እንግልት በመፍራት ከሙያው እና ከሀገር እየራቁ ይገኛሉ፡፡
ተቋሙ አክሎም ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ አባይ ዘውዱ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ቴዎድሮስ ዘርፉ፣ መስከረም አበራ፣በቃሉ አላምረው እና ሌሎችም ለእስር ተዳርገዋል ያለ ሲሆን መንግስት ጋዜጠኞቹን ከእስር እንዲለቅም ጠይቋል፡፡