አሜሪካ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠየቀች

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የሚገኘውን የአሜሪካ ግቢ ጎብኝተዋል።

አምባሳደሩ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት የአሜሪካ ግቢ ከ87 አመት በፊት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ከሞት ማምለጫ መሆኑን አውስተዋል።

የካቲት 12 1929 ዓ.ም ፋሺስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት ጭፍጨፋ ሲፈጽም አሜሪካዊው ዲፕሎማት ኮርኔልስ ቫን ኤንገርት ከ750 በላይ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲው ውስጥ እንዲደደበቁ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ከ87 አመት የሰውነት ክብራቸው ተጥሶ በህይወት የመኖር መብታቸው ሲነጠቅ ታይቷል ያሉት አምባሳደሩ የሞራል ልዕልና እና ሰብአዊነት ካላቸው ኮርኔልስ ቫን ኤንገርት ልንማር ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል።

ከ87 አመት በኋላም በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት የሰው ልጆች ክብር እና በህይወት የመኖር መብት በታጣቂዎች፣ ዘራፊ ቡድኖች እንዲሁም በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መጣሳቸው መቀጠሉ ከታሪክ አለመማራችን ያሳያል ብለዋል።

በጦርነት እና ግጭት ወቅት ጭምር የሰው ልጆች ክብርና ሰብአዊ መብት ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚገባ በማሳሰብም ኢትዮጵያውያን ካለፈ ታሪካቸው ሊማሩ ይገባል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶችንም በንግግር መፍታትና ንጹሃንን ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የታጠቁ ሃይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በንግግር ከመፍታት ይልቅ ጦር መስበቃቸውና መንግስት ይህን ለማስቆም የሚወስዳቸው እርምጃዎች መጠንከር የውይይት በሩን እየዘጋው እንዳይሄድም ስጋታቸውን አክለዋል።

የንጹሃን ግድያ፣ ከህግ ውጪ የሚፈጸም እስርና መሰወር እንዲሁም ከግጭቶች ጋር የተያያዙ አስገድዶ መድፈር መበራከት በአፋጣኝ እንዲቆምና በሽግግር ፍትህ አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑም አምባሳደሩ አሳስበዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳሰው የኦሮሚያ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት ኦነግ ሸኔ እያለ የሚጠራው) ሃይል በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከመንግስት ጋር ጀምሮት ወደነበረው ድርድር እንዲመለስ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልልም የፋኖ ታጣቂዎች መንግስት ያቀረበላቸውን የድርድር ጥያቄ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ህወሃትም ከአማራ ክልል ጋር የሚወዛገብባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ በንግግር መፍታት እንጂ ሃይል አማራጭ እንደማይሆን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገባችበትን ችግር ለመፍታት ብሄራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህን ማስፈን ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስም አሜሪካ ለዚህ ጥረት ድጋፏን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *